የሰብዓዊ አገልግሎት ትብብርን በማጠናከር ለተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች የተጋለጡ ወገኖችን መደገፍ ይገባል - ማኅበሩ - ኢዜአ አማርኛ
የሰብዓዊ አገልግሎት ትብብርን በማጠናከር ለተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች የተጋለጡ ወገኖችን መደገፍ ይገባል - ማኅበሩ
አዳማ፤ ሚያዚያ 30/2017(ኢዜአ)፡- የሰብዓዊ አገልግሎት ትብብርን በማጠናከር ለተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች የተጋለጡ ወገኖችን መደገፍ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አመለከተ።
"ሰብዓዊነትን እናፅና" በሚል መሪ ሀሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ67ኛ ጊዜ የዓለም የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ቀን በአዳማ ከተማ በእግር ጉዞና በፓናል ውይይት ተከብሯል።
በመርሃ ግብሩ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ዋና ፀሐፊ አቶ አበራ ሉሌሳ እንዳሉት ማህበሩ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ለጉዳት ለተጋለጡ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።
ቀኑ በእግር ጉዞ የተከበረበት ዋና ዓላማ በማህበሩ ሠራተኞችና አባላት፣ በበጎ ፈቃደኞች እንዲሁም በባለድርሻና አጋር አካላት መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከር መሆኑን ጠቁመዋል።
እንዲሁም የአሁንና የወደፊት የሰብዓዊ አገልግሎት ትብብርን ለማጎልበት እና የማህበሩን ገጽታ ለማሳደግ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ማህበሩ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት የዘረጋቸው የድጋፍ ማሰባሰቢያ ዘዴዎችን በመጠቀም ሁሉም አካል ለማህበሩ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሀመድ ጀማል በበኩላቸው ማህበሩ ባለፉት ዓመታት በክልሉ የአምቡላንስና መሠረታዊ የመድሀኒት አገልግሎትን ጨምሮ በርካታ ሰብዓዊ አገልግሎቶችን ለህብረተሰብ መስጠቱን አስታውሰዋል።
ለቆምንለት እና ለምንኖርለት የሰብዓዊነት አገልግሎት ሁልጊዜ የቀይ መስቀል መሠረታዊ መርሆችን አክብረንና ተገዢ ሆነን ሥራችንን እናስፋፋለን ብለዋል።
በመድረኩ የተገኙት የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ተወካይና የኮሙኒኬሽን የሥራ ሂደት ምክትል ኃላፊ አቶ ዘውዱ አያሌው ቀይ መስቀል ያለአድልዎ እርዳታ የሚሰጥ የዓለም ትልቁ የሰብዓዊ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።
የቀይ መስቀል ሠራተኞች እራሳቸውን ለአደጋና ለጉዳት ጭምር እያጋለጡ ለሰብዓዊ አገልግሎት በቁርጠኝነት መሰለፋቸውን አውስተዋል።
የዓለም ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ማህበራት ፌዴሬሽን የኢትዮጵያና ጁቡቲ ተወካይ ሚሲስ ፓውላ ፊዜራልድ በበኩላቸው፣ ፌዴሬሽኑ ኢትዮዽያን ጨምሮ በተቀረው ዓለም ሰብዓዊ ድጋፍን ተደራሽ ለማድረግ የበኩሉን ለመወጣት ራዕይ ሰንቆ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በየዓመቱ ሚያዝያ 30 የሚከበረውን የዓለም ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ቀን ከሚያዚያ 27 ጀምሮ በሁሉም ክልሎች በተለያዩ መርሃ ግብሮች ሲከበር መቆየቱ ተገልጿል።
በዚህም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የማኅበሩ በጎ ፈቃደኞችና ሠራተኞች በዓሉን በጽዳት፣ በደም ልገሳ፣ ለአቅመ ደካሞችና በየሆስፒታሉ ተኝተው ለሚታከሙ ወገኖች ድጋፎችን በማድረግና ሌሎች በጎ ተግባራትን በማከናወን እንዳከበሩትም ታውቋል።