በተለያዩ ጊዜያት ለሚከሰቱ የሕብረተሰብ የጤና አደጋዎች በቂ ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በተለያዩ ጊዜያት ለሚከሰቱ የሕብረተሰብ የጤና አደጋዎች በቂ ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2017(ኢዜአ)፦ በተለያዩ ጊዜያት ለሚከሰቱ የሕብረተሰብ የጤና አደጋዎች በቂ ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ አቅሞች እየተፈጠሩ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከልን የአፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና የልህቀት ማዕከል እንዲሆን የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በመርኃ ግብሩ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ የዓለም ጤና ድርጅት እና የአፍሪካ ሲዲሲ ተወካዮችን ጨምሮ የክልሎች ጤና ቢሮ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት፤ በይፋ ስራ የጀመረው የልህቀት ማዕከል የቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ የዝግጁነት፣ የምላሽ አሰጣጥና የመልሶ ማቋቋም ስርዓቶችን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ማዕከሉ ባሉት የሰለጠኑ ባለሙያዎች፣ ዘመናዊ ላቦራቶሪዎች እንዲሁም ለአደጋ ጊዜ ባለው ዝግጁነት ወደ ልህቀት ማዕከልነት ማደጉን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ በየጊዜው ለሚከሰቱ የሕብረተሰብ የጤና አደጋዎች በቂ ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ አቅሞች እየተፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጠንካራ የጤና ስርዓትን በመገንባት ለሕብረተሰብ የጤና አደጋዎች በቂ ምላሽ የመስጠት አቅም ማደግ እንደሚገባው ጠቁመው፤ የልህቀት ማዕከሉ ለአፍሪካ ሀገራት የአቅም ግንባታ ስራዎችን እንደሚያከናውንም ጠቁመዋል፡፡
የልህቀት ማዕከሉ በቀጣይ የሰው ሀይል ስልጠናና አቅም ግንባታ፣ የመሰረተ ልማትን የማዘመን ስራዎች፣ ዲጂታላይዜሽን፣ የአስተዳደርና የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ አመቺ ሁኔታዎችን መፍጠር ላይ እንደሚሰራም ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሃይሉ በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሽታዎችን የመከላከል አቅምና ዝግጁነት እንዲሁም የተጋላጭነት ስጋት ዳሰሳዎችን ይሰራል ብለዋል፡፡
እንዲሁም የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በበለጠ ለመቆጣጠር የጤና ስርዓቱ አቅም እንዲኖረው ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በመረጃ ላይ የተመሰረተ የአቅም ግንባታ፣ አዳዲስ ፈጠራዎች እና ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ስርዓት መገንባት፣ የግብዓት አቅርቦትን ማሻሻል እና ማዘመን በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ይሰራል ተብሏል፡፡
የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከል ማዕከል የአደጋ ዝግጁነትና ምላሽ ሃላፊ ዶክተር ወሳም ማንኮላ ማዕከሉ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካና ጎረቤት ሀገራት ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
ማዕከሉ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ ሀገራት በማዕከልነት እንዲያገለግል አሁን ካለው አቅም በተሻለ መልኩ መደራጀት የሚያስችል ዝርዝር ገለጻ ለዓለም ጤና ድርጅት፣ ለአፍሪካ ሲዲሲ እንዲሁም ለሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቅረቡ ተመላክቷል፡፡