የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሰራር ስርዓቱን የሚያዘምኑ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል-ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሰራር ስርዓቱን የሚያዘምኑ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል-ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 30 /2017 (ኢዜአ)፦የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አገልግሎቱን ፍትሀዊና ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር የአሰራር ሥርዓቱን ዘመናዊ እያደረገ መሆኑን ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የውጭ አገር የስራ ስምሪትን በሚመለከት ያካሔደውን ጥናት ይፋ ለማድረግ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
ውይይቱን አስመልክቶ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሚኒስቴሩ የአሰራር ስርዓቱን የሚያዘምኑ በርካታ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል።
በተለይም ዘርፉን ከብልሹ አሰራር ለማላቀቅና ፍትሀዊነትን ለማስፈን በቴክኖሎጂያዊ የታገዘ አሰራርን ማስረፅ አንዱና ዋነኛው ነው ብለዋል።
በዚህም ህጋዊ የውጭ አገር የሥራ ስምሪትን ተደራሽ ከማድረግ በዘለለ የሥራ እድልን በመፍጠር ረገድ አበረታች ውጤት መምጣቱን አንስተዋል።
ይሁን እንጂ አሁንም የውጭ አገር የሥራ ስምሪትን በህገ ወጥ ኤጀንሲዎች በኩል የሚፈጸም መኖሩን ጠቁመው፤ ለዚህም የህግ ተጠያቂነትን ለማስፈን ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ይገኛል።
የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጉዳዩን በሚመለከት ያካሔደው ጥልቅ ጥናት ህገ ወጥ አሰራርን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ተጠያቂነትን ለማስፈን በእጅጉ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የጥናት ውጤቱን መነሻ በማድረግ ያሉ ክፍተቶችና ጉድለቶችን የማረም ሥራ በትኩረት እንደሚከናወን አፅንኦት ሰጥተዋል።
የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እሸቴ አስፋው በበኩላቸው፥መንግሥት ተቋማትን ለመፈተሽ የዘረጋው ግልጽ አሰራር ለሚደረገው የቁጥጥር ስራ አስቻይ ሁኔታ እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል።
ዛሬ ይፋ የሚደረገውና በውጭ አገር የሥራ ስምሪት ላይ የተካሄደው ጥናትም የዚሁ አካል መሆኑን አብራርተዋል።
ጥናቱን ተከትሎ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ኮሚሽኑ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ኮሚሽነሩ አረጋግጠዋል።
በቀጣይም በተለያዩ ተቋማት የተካሔዱ መሰል ጥናቶች ይፋ እንደሚደረጉም አክለዋል።
''የውጭ አገር የስራ ስምሪት ለሙስናና ብልሹ አሰራር ያለው ተጋላጭነት" በሚል ርዕስ በተካሔደው ጥናት ዙሪያ ውይይት የሚካሔድ ይሆናል።