ቀጥታ፡

ንቅናቄው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ከመተካት ባሻገር ወደ ውጭ ገበያ መላክ የሚያስችል አቅም ፈጥሯል-ሚኒስትር መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 30 /2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ከመተካት ባሻገር ወደ ውጭ ገበያ መላክ የሚያስችል አቅም መፍጠሩን የኢንዲስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

መንግስት የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያና የፖሊሲ እርምጃዎችን በመውሰድ የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም ማሻሻል ችሏል፡፡

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው፣የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲሁም ሌሎች ህጋዊ ማዕቀፎች የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው እምርታዊ ለውጥ እንዲያመጣ አግዘውታል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በምርት ጥራትና ገበያ ተወዳዳሪነት መሰረታዊ ለውጥ ተመዝግቧል፡፡

በአሁኑ ወቅት እየጠነከረ የመጣውን የዓለም የአምራች ኢንዱስትሪ ለመወዳደር ከደንበኞች ፍላጎት ጋር የሚሄዱ ምርቶችን የማመረት አቅም መጨመሩን ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ ንቅናቄው የቴክኖሎጂ ሽግግር በመፍጠር፣ክህሎትን በማሻሻል እና የጥሬ እቃ አቅርቦትን በጥራትና በዓይነት በማሳደግ ገንቢ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የግብዓት አቅርቦትን በማሻሻል የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ተወዳዳሪ ምርት የማምረት አቅም አሳድጓል ብለዋል፡፡

ለውጭ ገበያ ማምረት ላይ ብቻ የተንጠለጠለውን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ወደ ሁለገብ በመቀየር 96 የሚሆኑ የምርት ዓይነቶች በአገር ውስጥ ምርት መተካት የሚያስችል ስትራቴጂ በመንደፍ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ተናገርዋል፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በ2014 ዓ.ም ሲጀመር በዓመት መተካት የተቻለው 318 ሚሊዬን ዶላር ብቻ እንደነበር አስታውሰው፤ በተያዘው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ሦስት ነጥብ አንድ ቢሊዬን ዶላር ተተክቷል ብለዋል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ከመተካት ባለፈ ከአገር ውስጥ ፍጆታ በላይ የሆኑትን ለውጭ ገበያ ማቅረብ አስችሏል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የመኖ ማምረቻ ፋብሪካ በማምረት ወደ ጎረቤት አገራት እየላከች መሆኑን ገልፀው፤የተለያዩ ምርቶች ማሽነሪዎችን ለመላከ በሂደት ላይ ነን ብለዋል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪዎች ጥሬ እቃዎችን በአገር ውስጥ ማምረት በመጀመራቸው አቅርቦቱን ከማሻሻል ባለፈ ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡

በኢትዮጵያ የተመረቱ ምርቶችን የመጠቀም ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ሰፊ የህዝብ ቁጥር ያለው አገር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በአምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል ያለው የግብይት ቅብብሎሽ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በግሉ እና የመንግስት ተቋማት መካከል ያለው ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከሩን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም