ቀጥታ፡

በለውጡ ዓመታት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማጠናከር ረገድ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 30 /2017 (ኢዜአ)፦በለውጡ ዓመታት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማጠናከር ረገድ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የፌዴራል ባለድርሻ አካላት የትብብርና የቅንጅት መድረክን በተመለከተ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

በውይይቱ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የፌዴራል ተቋማት ተወካዮችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ፣ ሰላም ግንባታ እና ግጭት አፈታት፣ በዜጎች ተሳትፎና ተጠቃሚነት፣ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ፡፡

ድርጅቶቹ ሚናቸውን በላቀ ደረጃ እንዲወጡ መንግሥት በርካታ የሪፎርም ተግባራት ማከናወኑን ጠቁመው፤ በዚህም አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን አንስተዋል።

በተለይም አሳሪ ህጎችና አዋጆችን በማሻሻል ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተሻለ መንቀሳቀስ የሚችሉበት አውድ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር፣ በስራ ዕድል ፈጠራና ሌሎችም አገራዊ አጀንዳዎች ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑንም ነው ያነሱት።

በቀውስ ጊዜም አስቸኳይ ድጋፎችን በማስተባበርና ተደራሽ በማድረግ ረገድ ተጠቃሽ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ጠቁመው፤አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፏቸው ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል።

በአገር ግንባታ ሂደትም ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድርሻ የላቀ ሊሆን እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚጫወቱትን ሚና ይበልጥ እንዲያሳድጉ መሰል የቅንጅትና ውይይት መድረክ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግሥት ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድሬጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አህመድ ሁሴን በበኩላቸው፤ ቅንጅትና ትብብር መድረኩ ከፌዴራል እስከ ክልሎች ታችኛው መዋቅር ድረስ አደረጃጀት ያለው መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም መንግስት፣ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ለሰላም መስፈን፣ ለማህበረሰብ ተጠቃሚነት በጋራ የሚንቀሳቀሱበት መሆኑን ገልጸዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በበኩላቸው፥ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና በመንግሥት ተቋማት መካከል ቅንጅትን የሚያጠናክሩ ተግባራት ያከናውናሉ።

የዛሬው ውይይትም በቅንጅት እና ትብብሩ ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ እና መግባባት ላይ ለመድረስ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም