ቀጥታ፡

በሀድያ ዞን የተገነባ የገጠር መንገድ እና ድልድይ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

ሆሳዕና፤ሚያዚያ 30/2017 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀድያ ዞን በ31 ሚሊዮን ብር የተገነባ የገጠር መንገድ እና ድልድይ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።

ፕሮጀክቱን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ናቸው።

ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉት በክልሉ መንገዶች ባለስልጣን ሆሳዕና ዲስትሪክት ሀድያ ዞን የተገነባ የበሌሳ - ከቤቾ - ዶዕሻ የ15 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ እና ድልድይ ናቸው።

መንገዱ በሀድያ ዞን ሌም፣ አንሌሞንና ሻሸጎ ወረዳዎችን እንዲሁም የስለጤ ዞንን የሚያገናኝ መሆኑም ተመላክቷል።

ለመንገዱና ድልድይ ግንባታ ሥራ ከ31 ሚሊዮን 300 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን ወጪው በክልሉ መንገዶች ባለስልጣን መሸፈኑም ታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በሀድያ ዞን አመካ ወረዳ በ125 ሚሊዮን ብር የተገነቡት ሁለት የመስኖ ፕሮጀክቶችና ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የእመዣር - ዱና- ሌራ 20 የኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ ፕሮጀክት እንደሚመረቅም ተጠቁሟል፡፡

ሁለቱ የመስኖ ፕሮጀክቶች 270 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያላቸው ሲሆን 980 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ በብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም