የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ ነው

አዳማ፤ሚያዚያ 30/2017 (ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ መሆኑን የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም ገለጹ።

ኢዜአ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከደን ልማት አኳያ የሚያስገኘው ፋይዳ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ደን ልማት እና ከአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ኮሚቴ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ቆይታ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባት ከያዘቻቸው እቅዶች መካከል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዋነኛው ነው።

መርሃ ግብሩ ከዚህ በፊት በተፈጥሮ ደን ላይ ሲደርስ የነበረውን ጉዳት ከመከላከል ባለፈ የደን ሽፋንን እያሳደገ መምጣቱንም አመልክተዋል።

ከዚህ ቀደም በተፈጥሮ ደኖች ላይ ከፍተኛ ጭፍጨፋ ሲደርስ እንደነበር አስታውሰው፥ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ወዲህ ግን የማገዶና የግንባታ ግብዓት ፍላጎትን ከማሟላት ባሻገር በደን ሀብት ላይ የሚደርሰው ጉዳት በእጅጉ እንዲቀንስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብራርተዋል።

መርሃ ግብሩ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ ከማድረግ ባለፈ ወንዞች ዓመቱን ሙሉ ተመጣጣኝ ፍሰት እንዲኖራቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ማስገኘቱን አውስተዋል።

በተለይም ሥነ ምህዳር እንዲጠበቅና የእርሻ መሬት ከጎርፍ እንዲጠበቅ ጉልህ ሚና ማበርከቱን ጠቅሰው፥ በየዓመቱ 92 ሺህ ሄክታር ደን ላይ ሲደርስ የነበረውን ጭፍጨፋ ባለፈው ዓመት በተጠናው ጥናት መሠረት ወደ 27 ሺህ ሄክታር በመቀነሱ ከፍተኛ ስኬት መሆኑን አቶ ከበደ አስታውቀዋል።

በተለይ የሚተከለው ችግኝ በውጭ ምንዛሬ የሚገባውን የጣውላና ሌሎች የእንጨት ምርትን በመተካት ረገድ ተስፋ የሚጣልበት ነው ሲሉ አስረድተዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አደፍርስ ወርቁ(ዶ/ር) በበኩላቸው፥ በመርሃ ግብሩ ባለፉት ዓመታት ከተተከሉት ችግኞች ውስጥ የሀገሪቱን የደን ሽፋን ለማሳደግ የሚያስችሉ ከ40 እስከ 48 በመቶ የሚሆኑት የደን ዝርያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህም ብዝሃሕይወት እንዳይጠፋ፣ የደን ሽፋን በማሳደግ እና ሀገር በቀል ዕፅዋት ዝርያዎችን ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ምትክ የለሽ መሆኑን አውስተዋል።

መርሃግብሩ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሚያስፈልጉ የእንጨት ግብዓቶችን ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ ለማምረት ጭምር ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።

ከዘላቂ ደን ልማት አንጻርም ዘንድሮ ለመትከል ከተዘጋጁት ችግኞች ውስጥ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን የሚሆኑት ሀገር በቀል የደን ዛፍ ዝርያዎች እንዲሆኑ ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።

ይህም ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቁመው፥ በተለይ ሊጠፉ የተቃረቡና የተመናመኑ ሀገር በቀል የዕፅዋት ዝርያዎችን በመታደግ አካባቢያዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዳለው አደፍርስ(ዶ/ር) ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም