ጠንካራ ቤተሰብ በመገንባት የጎለበተ ማህበረሰብ ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
ጠንካራ ቤተሰብ በመገንባት የጎለበተ ማህበረሰብ ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቷል
አዳማ፤ ሚያዝያ 29/2017(ኢዜአ)፦ጠንካራ ቤተሰብ በመገንባት በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፍ የጎለበተ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴሩ ''የተሻሻለ የቤተሰብ ሥራና ገቢ ለሀገር ኢኮኖሚ'' በሚል መሪ ሀሳብ ዘንድሮ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀን አስመልክቶ ለሚዲያና ባለድርሻ አካላት ያዘጋጀው የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ ዓሊ በተለይም ለኢዜአ እንዳስታወቁት መንግሥት የቤተሰብን ደህንነትና ምርታማነት ለማስጠበቅ ፖሊሲዎችና መዋቅሮችን በመዘርጋት እየሰራ ይገኛል።
ለዚህ ሲባል ሚኒስቴሩ የሥራ ክፍል በማደራጀትና የሠው ኃይል ከመመደብ ባለፈ ክልሎችና ባለድርሻ አካላትም በተመሳሳይ ሚናቸውን እንዲወጡ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀን ሲከበርም የቤተሰብን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ለማሳደግ፣ለችግር የተጋለጡ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለማሰብና ለመደገፍ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
በሚኒስቴሩ የአረጋዊያንና ቤተሰብ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ሮበሌ በበኩላቸው ቤተሰብ የማህበረሰብና የሀገር መሠረት በመሆኑ ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባል ብለዋል።
ቤተሰብ አምራች ሲሆን አገር ምርታማ ትሆናለች ያሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ በተለይም ሀገር እንዲፀና የቤተሰብ ሁለንተናዊ ብልጽግና፣ ደኅንነት እና ዘላቂነት ሊረጋገጥ እንደሚገባ አስረድተዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ አየሁ ደመቀ በሰጡት አስተያየት ሀገር በኢኮኖሚ ሊገነባና ሊያድግ የሚችለው ቤተሰብ በመልካም ሰብዕና የታነፀ ትውልድ መተካት ሲችል ነው።
በመሆኑም የቤተሰብ ቀን ሲከበር ቤተሰብ እንደ አንድ ወሳኝ ተቋም በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተገቢ ሚናውን እንዲወጣ ያስችላል ብለዋል።