ቀጥታ፡

የተገኘውን ሰላም በማዝለቅ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል የሚጠበቅብንን ኃላፊነት እንወጣለን

ወልዲያ፤ሚያዝያ 29/2017 (ኢዜአ)፦በአካባቢያቸው የሰፈነውን ሰላም በማዝለቅ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ በወልዲያ ከተማ ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች እና በደብረ ማርቆስ ከተማ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች ገለፁ።

በከተሞቹ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ህዝባዊ ውይይቶች ዛሬ ተካሂደዋል።

የመድረክ ተሳታፊዎቹ እንደገለፁት፥ ሁሉም አካባቢውን ከመጠበቅ ባለፈ በየተሰማራበት መስክ ጠንክሮ በመስራት በመንግስትና በህዝብ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ሊያግዝ ይገባል።

በወልዲያ ከተማ ዙሪያ አርሶ አደር አስፋው ሹሙ ሰላም ከሌለ አርሶ መብላትም ሆነ ወልዶ መሳም አይቻልም ካሉ በኋላ ሁሉም የተገኘውን ሰላም በማፅናት በልማት ስራው ላይ ሊሳተፍ ይገባል ብለዋል።

በዚህም መንግስት በአካባቢው እያከናወነ ያለውን የልማት እንቅስቃሴ በመደገፍ ረገድ የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት ተዘጋጅተናል ነው ያሉት።

የአካባቢው አርሶ አደሮች ያገኘነውን ሠላም ዘላቂ ለማድረግ የአቅማችንን ለማድረግ ዝግጁ ነን ያሉት ደግሞ አቶ ተገኘ ማስረሻ ናቸው።

የወልዲያ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ በበኩላቸው፥ አርሶ አደሩ በወቅቱ እንዳይዘራ፣ ማዳበሪያ እንዳይወስድ፣ ልጆቹ ከፍርሃት ነጻ ሆነው እንዳይማሩ በፅንፈኛው ኃይል ሲታወክ መቆየቱን ገልፀዋል።

አሁን ላይ አመራሩ ከጸጥታ ሃይሉ ጋር በመቀናጀት ባደረገው ጥረት የመጣውን ሰላም ዘላቂነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት አርሶ አደሩ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እንዲወጣ አሳስበዋል።

በተመሳሳይም በደብረ ማርቆስና አካባቢው የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች የሰፈነውን ሰላም በዘላቂነት በማጽናት የልማት ስራዎችን በማጠናከር ረገድ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የሆኑት አቶ ገነት ያዜ እንዳሉት መንግስት ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ማህበረሰቡን ከማወያየት ጀምሮ እያደረገ ያለው ትግል የሚደነቅ ነው።

አሁን በተገኘው ሰላም በነጻነት ወጥተን መግባት ችለናል ያሉት አቶ ገነት በቀጣይ በየተቋማችን የአገልግሎት አሰጣጣችንን በማሻሻል ሰላሙን ለማጽናት እንሰራለን ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፥ የደብረ ማርቆስ ከተማ ከነበረችበት ችግር እንድትወጣ የመንግስት ሰራተኞች ሚና የጎላ ነበር ብለዋል።

አሁንም ዘላቂ ሰላም ሰፍኖ የተጀመሩ የልማት ስራዎች በተሻለ እንዲጠናከሩ ለማድረግ የመንግስት ሰራተኛው እየተወጣ የሚገኘውን ኃላፊነት ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም