የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ያሰባሰባቸውን አጀንዳዎች ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረከበ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ያሰባሰባቸውን አጀንዳዎች ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረከበ
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 29/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ለሀገራዊ ምክክሩ ግብአት የሚሆኑ ከመላው ሀገሪቷ የተሰባሰቡ አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ አስረክቧል።
አጀንዳዎቹን የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ አስካለ ለማ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ አስረክበዋል።
አጀንዳዎቹ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተሰበሰቡና ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች እና በሴቶች እኩል ተጠቃሚነት ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ሚናውን ሲወጣ መቆየቱን አስታውሰው፥ በቀጣይም ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ ልማት፣ሰላምና ዴሞክራሲ መረጋገጥ የበኩሉን ይወጣል ሲሉም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ መሰረታዊ እና ሀገራዊ በሆኑ አጀንዳዎች የሚታዩ የሀሳብ ልዩነቶችና አለመግባባት መንስኤዎችን ለመለየት የሚያስችል አጀንዳ በመቅረጽ ምክክር እንዲደረግባቸው የማድረግ ዓላማ አንግቦ እየሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም ልዩነት በተፈጠረባቸው ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት የሚፈጠርበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በተቋማትና በማህበረሰብ ክፍሎች ተደራጅተው የሚቀርቡ አጀንዳዎችን በአግባቡ እንደሚጠቀምባቸውም ጠቁመዋል፡፡