ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ሕልሞች ለማሳካት ሁሉም በላቀ ደረጃ የድርሻውን መወጣት አለበት - ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን የብልጽግና ሕልሞች ለማሳካት ሁሉም በላቀ ደረጃ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) አሳሰቡ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሠራተኞችና አመራሮች “የመሐል ዘመን” በሚል ርእስ በተዘጋጀው ሀገራዊ ሰነድ ላይ ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት ተቋማትና ግለሰቦች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት፣ በጥራትና ወቅቱ በሚጠይቀው አግባብ ከተወጡ የኢትዮጵያ የብልጽግና ሕልሞች የሚሳኩ ስለመሆናቸው ያለፉት ዓመታት ስኬቶች ምስክሮች ናቸው።


 

የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የተሰጠው ኃላፊነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ማስገንዘብ፣ የመንግሥትን ፖሊሲዎች፣ መነሣሣቶች፣ ዕቅዶች፣ አፈጻጸሞችና ውጤቶችን ማሳወቅ መሆኑንም አመላክተዋል።

ዘርፉን በአጀንዳ መምራትና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ የሚመዘዙ አጀንዳዎችን በብቃት መመከት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አስገንዘብበዋል።

የመሐል ዘመን በሚል ርእስ የመወያያ ሰነዱን ያቀረቡት የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት ከነበረችበት ሁኔታ መሰረታዊ በሆነ መልኩ እድገት እያስመዘገበች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ይህንን ለውጥ ወደ ፊት ለማስቀጠልና ወደማይቀለበስበት ደረጃ ለማድረስም በውስጥና በውጭ ያሉ ክፍተቶችንና ተጋላጭነቶችን ነቅሶ በማውጣት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።


 

ሃገራችን በለውጥ ሂደት ያለፈችው የለውጡን ቀልባሽ ኃይሎች በመርታት ብቻ አይደለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ፈተናዎችን ጭምር መሻገሯን አስረድተዋል።

ድርቅ፣ የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽ፣ የእርስ በርስ ግጭትና መፈናቀል ለውጡን የፈተኑ ጉዳዮች እንደነበሩም አንስተዋል።

የሕዝቡ ፍላጎት፣ የለውጡ አመራር ቁርጠኝነትና የሰጠው ብስለት የተሞላበት አመራር የተገኘውን ለውጥ ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገራቸውንም አቶ ተስፋሁን አብራርተዋል።

የሕዝብን ጥያቄዎች በመመለስ፣ አካታች የፖለቲካ ሥርዓት በመዘርጋት፣ በኢኮኖሚ ሪፎርምና ዕድገቱን በማስቀጠል፣ የትርክት ለውጥ በማድረግና ፈተናዎችን በመቋቋም በርካታ ስኬቶች በየዘርፉ መመዝገባቸውን አቶ ተስፋሁን ገልጸዋል።

 

ይሁን እንጂ እነዚህ ስኬቶች የፈጠሩት መለስተኛ እርካታ ወደማይቀለበሰው የብልጽግና መዳረሻ የሚደረገውን ጉዞ እንዳያሰናክሉ በብስለት ማለፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በስኬቶች ሊደበቁ የሚችሉ ውስጣዊ ክፍተቶችን ያለማቅማማት መፍታት እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

በውይይቱ የተሳፉት የአገልግሎቱ አመራር እና ባለሙያዎች ሰነዱ በርካታ ጉዳዮችን የዳሰሰና ተጨባጭ ሁኔታውን ያገናዘበ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገራዊ የለውጥ ጉዞው ያለበትን ደረጃና ቀጣይ የሚጠይቀውን ጥረት በእጅጉ እንደተረዱበትም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም