በየደረጃው ያሉ የሰራዊቱ አመራሮች የግዳጅ አፈጻጸም፣ የመምራትና የመፈጸም አቅም በላቀ መልኩ እየተገነባ ነው - ሌተናል ጀነራል መሐመድ ተሰማ - ኢዜአ አማርኛ
በየደረጃው ያሉ የሰራዊቱ አመራሮች የግዳጅ አፈጻጸም፣ የመምራትና የመፈጸም አቅም በላቀ መልኩ እየተገነባ ነው - ሌተናል ጀነራል መሐመድ ተሰማ
ባህር ዳር፤ ሚያዚያ 29/2017(ኢዜአ)፡-በየደረጃው ያሉ የሰራዊቱ አመራሮች የግዳጅ አፈጻጸም፣ የመምራትና የመፈጸም አቅም በላቀ መልኩ እየተገነባ መሆኑን የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል መሐመድ ተሰማ ገለጹ።
ሌተናል ጀነራሉ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተሰማርተው ተልእኮና ግዳጃቸውን እየተወጡ ለሚገኙ የሰራዊቱ አመራሮች የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።
ሌተናል ጀነራል መሀመድ በሰጡት መመሪያ በየደረጃው ያሉ የሰራዊቱ አመራሮች የግዳጅ አፈጻጸም፣ የመምራትና የመፈጸም አቅም በላቀ መልኩ እየተገነባ መሆኑን አንስተዋል።
በተለያዩ ወታደራዊ እውቀቶችና ቴክኖሎጂዎች ጭምር የሚታገዝ ጠንካራ አመራር በመፈጠሩ በየትኛውም ግዳጅና ተልእኮ በላቀ ብቃት የመምራትና የመፈጸም አቅም ተፈጥሯል ብለዋል።
በመሆኑም በየደረጃው ያሉ የሰራዊቱ አመራሮች የጨበጡትን ዕውቀት፣ ብቃት እና ክህሎት በአግባቡ መተግበራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
የሰራዊቱ ግዳጅ አፈጻጸም በሀላፊነትና በዲስፕሊን የሚመራ ስለመሆኑ አንስተው ሀገራዊ ተልእኮን በላቀ ብቃትና ጀግንነት ማከናወኑ የሁል ጊዜም ግብ ሆኖ መቀጠል አለበት ሲሉም ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በየትኛውም ቦታ ተልእኮውን በላቀ ብቃት መፈፀም የሚችል የድል ሰራዊት ስለመሆኑም ገልጸዋል።
በመሆኑም በስልጠና ላይ የነበሩ የሰራዊቱ አመራሮች የተሰጠው የአመራርነት፣ የስነ-ልቦና፣ የተኩስ፣ የአካል ብቃትና ሌሎችም ወታደራዊ ስልቶችን እስከ ታች ድረስ በማስረፅ ለላቀ የአላማ ስኬት እንዲዘጋጁ ሌተናል ጀነራል መሀመድ አሳስበዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ አሰተያየታቸውን የሰጡ አመራሮችም ለሀገራቸው ክብርና ሉአላዊነት የሚጠበቅባቸውን ሁሉ በላቀ ጀግንነት ለመፈፀም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
አሁን ላይ በየደረጃው ያለው የሰራዊቱ አመራር የመሪነት ብቃትና የሰራዊቱ አባላት በጠንካራ ቁመና ላይ የሚገኝ መሆኑንም ገልጸዋል።