የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ላቦራቶሪ የምርመራ አገልግሎት መስጠት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ላቦራቶሪ የምርመራ አገልግሎት መስጠት ጀመረ
ወራቤ፤ ሚያዝያ 29/2017(ኢዜአ)፡-የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ላቦራቶሪ ተመርቆ የምርመራ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
ላቦራቶሪውን በወራቤ ከተማ ተገኝተው ዛሬ መርቀው ሥራ ያስጀመሩት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ እና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሳሮ አብደላ ናቸው።
በክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የላቦራቶሪ ምርመራ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ወንድሙ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የላቦራቶሪው ሥራ መጀመር በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰቱ የጤና እክሎችን በሕክምና አገልግሎት ለመከላከል ያስችላል።
የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ እና የቲቢ በሽታ የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመለየት ለታካሚዎች ተገቢ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
እንዲሁም ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በአግባቡ ለይቶ ለማከም ላቦራቶሪው ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፣ ይህም ከዚህ ቀደም ህብረተሰቡ የላቦራቶሪ ምርመራ ለማሰራት ወደሌሎች አካባቢዎች በመሄድ ይደርስበት የነበረውን እንግልት ያስቀራል ብለዋል።
ላቦራቶሪውን ለአገልግሎት ለማብቃት ከክልሉ መንግስት፣ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ከተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ መደረጉንም አቶ ግርማ ተናግረዋል።
ከግብረሰናይ ድርጅቶች ግምቱ 200 ሺህ ዶላር የሚሆን የማሽንና መሰል ግብአቶች ድጋፍ መደረጉን የገለጹት አቶ ግርማ፣ የክልሉ መንግስትም 10 ሚሊዮን ብር ለግብአት ማሟያ እገዛ እድርጓል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም የሰው ኃይል በማሰልጠን፣ ለመመርመሪያ መሳሪያዎች ተስማሚ የሆነ የሙቀት ምህዳር መሳሪያ (ኤሲ) በመግጠምና ላቦራቶሪው ወደስራ እንዲገባ በማገዝ ድጋፍ ማድረጉን አስረድተዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ፣ የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን እንዲሁም የክልሉና የዞን ከፍተኛ አመራሮችም ተገኝተዋል።