የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ስኬት ማሳያ ነው - ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ስኬት ማሳያ ነው - ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2017(ኢዜአ)፦ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ስኬት ማሳያ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለፀ።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተመርቆ ስራ መጀመሩ ይታወቃል።
ማዕከሉ በአንድ ጣራ ስር የተለያዩ የመንግስት አገልግሎቶችን በማጣመር የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሚሰጥ አገልግሎት ነው።
ማዕከሉ ዜጎች የተሟላ የዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም በቀላሉ የተለያዩ የፌዴራል ተቋማትን አገልግሎቶች እንዲያገኙ የሚያስችል ሲሆን 12 ተቋማት ተቀናጅተው ከ41 በላይ አገልግሎቶችን እየሰጡ ይገኛሉ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን አለማየሁ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ማዕከሉ በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ላይ በመስጠት ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል ነው።
ይህም የአገልግሎት አሰጣጥ ባህልን የሚያሳድግ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ከ800 በላይ የመንግስት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ማድረግ መቻሉን ገልፀው፤ ይህም የአገልግሎት አሰጣጥን ውጤታማነትን የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ስኬት ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን ማሳካት የሚያስችሉ ስራዎች መሰራታቸውንና የኢንተርኔትና ኤሌክትሪክ አቅርቦትና ተጠቃሚነት መስፋፋቱን ብሎም የዳታ ማዕከላት እየተገነቡ መሆኑን አብራርተዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ከአጋርና የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እየተዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል።