የኢትዮጵያ መድን እና የባህር ዳር ከተማ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መድን እና የባህር ዳር ከተማ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 29/2017 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን እና ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ መድን በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 25 ጨዋታዎች 16 ጊዜ ሲያሸንፍ 3 ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። 6 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
34 ግቦችን ሲያስቆጥር 10 ግቦችን አስተናግዷል። በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው መድን በ54 ነጥብ የሊጉን አናት ላይ ተቀምጧል።
ተጋጣሚው ባህር ዳር ከተማ በሊጉ ባካሄዳቸው 25 ጨዋታዎች 12 ጊዜ ሲያሸንፍ 6 ጊዜ ተሸንፏል። 7 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።
በጨዋታዎቹ 30 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 14 ግቦችን አስተናግዷል። በደግአረገ ይግዛው የሚሰለጥነው ባህር ዳር ከተማ በ43 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ኢትዮጵያ መድን ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ያጠናክራል።
በአንጻሩ ባህር ዳር ከተማ ማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ እንዲያደርግ እና ከመሪው ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት እንዲያጠብ ያስችለዋል።
በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙት ክለቦች የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላኛው የ28ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ወላይታ ድቻ ከአርባምንጭ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
ወላይታ ድቻ በ38 ነጥብ 7ኛ፣ አርባምንጭ ከተማ በ35 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዘዋል።