ቀጥታ፡

በግዕዝ ቋንቋ የተጻፉ ስራዎችን በመተርጎም ለሀገራዊ ጥቅም ለማዋል ጥረት እየተደረገ ነው

ደሴ፤ ሚያዚያ 28/2017(ኢዜአ)፡-በግዕዝ ቋንቋ የተጻፉ ስራዎችን በመተርጎም ለሀገራዊ ጥቅም ለማዋል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የወሎ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ከወሎ ዩኒቨርሲቲና ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር 8ኛውን የግዕዝ ጉባኤ በወሎ ዩኒቨርሲቲ እያካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ተወካይ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃን አስማሜ፣ ዩኒቨርሲቲው የግዕዝ ቋንቋን በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ ትምህርት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

የግዕዝ ቋንቋ ከኢትዮጵያ አልፎ አሁን ላይ በተለያዩ የአለም አገራት የስልጣኔ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመው ዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር ጭምር በቋንቋው የተጻፉ ስራዎችን በመተርጎም ለሀገራዊ ጥቅም ለማዋል እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር ዮሐንስ አድገህ፤ የግዕዝ ቋንቋ ታሪክን ለማወቅና ለማጥናት፣ ለስነ ፈለግ፣ ለስነ ምድር፣ ለስነ ህክምና፣ ለስነ ምርምርና ሌሎችም ስራዎች ትልቅ አበርክቶ እንዳለው አስረድተዋል።

በዓለም ላይ ከሚገኙ ጥንታዊና የደረጀ ስርዓተ ፅህፈት ካላቸው ቋንቋዎች መካከል ግዕዝ አንዱ መሆኑን ጠቁመው ለዓለም እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ በጥናት በማስደገፍ መሰነድና ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ይኩኖአምላክ መዝገቡ፤ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ተጠብቀው፣ አድገውና ተስፋፍተው ለትውልድ እንዲተላለፉ በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድርብ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በዚህ ረገድ የወሎ ዩኒቨርሲቲ እያደረገ ላለው አስተዋጽኦ አድንቀው የኢትዮጵያን እምቅ ሃብቶች ለማሳደግ በጋራ መስራት ይገባናል ብለዋል።

የግዕዝ ቋንቋን መጠበቅና ማስፋፋት የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ስነ-ጥበብ፣ ስነ-ጽሁፍ፣ ስልጣኔና እድገት ትውልዱ መረዳት እንዲችል መስራት አስፈላጊ ስለመሆኑም አንስተዋል።

በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የግእዝ ቋንቋ ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው በቋንቋው የተጻፉ ጥንታዊ ጽሁፎችን በቤተ-መጻሕፍት በማስቀመጥ፣ በተለያዩ ቋንቋዎች በመተርጎም ህብረተሰቡ እንዲረዳቸው፣ ለጥናትና ምርምርም እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ ላይ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ የሐይማኖት አባቶችና ሌሎችም እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም