ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና እስራኤል የረጅም ጊዜ አጋርነታቸውን በኢኮኖሚ መስክ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና እስራኤል የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲ አጋርነታቸውን በኢኮኖሚ መስክ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታወቁ።

የኢትዮጵያ እና የእስራኤል የንግድ ፎረም ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመርኃ ግብሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር)፣ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ሰአር፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሀም በላይ(ዶ/ር) በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አቭራሃም ንጉሴ(ዶ/ር)፣ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የእስራኤል የቢዝነስ ልዑክ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር)፣ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በግብርና፣ በውኃ አስተዳደር፣ በጤና፣ በመከላከያ፣ በቴክኖሎጂ እና ትምህርት ዘርፎች ላይ እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።

የቢዝነስ ፎረሙ በኢኮኖሚ ዘርፍ ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሥራ ፈጠራ እና በጋራ መማማር ላይ ያተኮረ የረጅም ጊዜ አጋርነትን የመገንባት ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

የማሳቫ እስራኤል ኤጀንሲ ለኢትዮጵያ ገበሬዎች በመስኖ፣ ማዳበሪያ አመራረትና በዘመናዊ የግብርና አሰራሮች ላይ ለሰጠው ስልጠናና ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

የትብብሩ ተስፋ ሰጪ ውጤት ኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ በምትልከው የአቮካዶ ምርት ላይ በተጨባጭ መታየቱን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ያላትን የማይናወጥ አቋምም አረጋግጠዋል።

የእስራኤል የንግዱ ማህበረሰብም በኢትዮጵያ ኢንቨስት ከማድረግ ባለፈ የበለፀገ የወደፊት ሁኔታን ለመቅረፅ በጋራ እንስራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ሰአር በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና እስራኤል የቆየ እና ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የእስራኤል የንግድ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ጠንካራ ገበያ እና ኢኮኖሚ መመስረት እንደሚቻል አመላካች መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ህልሟን ለማሳካት በምታደርገው ጉዞ እስራኤል የስኬቱ አካል የመሆን ፍላጎት እንዳላትም አብራርተዋል።

የሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት ለኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸው መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም