በከተማው የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ውጤት እያመጣ ነው - የጎንደር ከተማ አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
በከተማው የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ውጤት እያመጣ ነው - የጎንደር ከተማ አስተዳደር
ጎንደር ፤ ሚያዝያ 28/2017(ኢዜአ)፡-በጎንደር ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር የትምህርት አቀባበል በማሻሻልና መጠነ ማቋረጥን በመቀነስ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።
የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ 11 ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው።
በመርሃ ግብሩም ከሶስት ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ህብረተሰቡና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ለመርሃ ግብሩ መሳካት በገንዘብና በቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በሙከራ ደረጃ የተመጀመረው የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር በቀጣይም በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ ሁሉም የቅድመና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የምገባ መርሃ ግብሩ በተማሪዎች የትምህርት አቀባበል ላይ እንዲሁም መጠነ ማቋረጥን በመቀነስ ረገድ ያመጣውን ለውጥ ለማረጋገጥ የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት በየትምህርት ቤቶቹ መካሄዱንም አስረድተዋል።
የመሰረት አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ስጦታው አምሃ እንዳሉት፤ በዘንድሮ ትምህርት ዘመን በትምህርት ቤታቸው ከ500 በላይ ተማሪዎች የምግባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
የምገባ መርሃ ግብሩ መጀመር አምና ትምህርት አቋርጠው የነበሩ ከ100 በላይ ተማሪዎች ዳግም እንዲጀምሩ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከ230 በላይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ህጻናት ተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብሩ ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የህብረት ቅድመና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አሻግሬ ለምለሙ ናቸው፡፡፡
የምገባው ተጠቃሚ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠውም ሆነ አርፍደው የመጡበት ሁኔታ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡
ለክልሉና ለከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በከተማው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በትምህርት ዘመኑ እየተከናወነ ስለሚገኘው የምገባ መርሃ ግብር ገለጻና ማብራሪያ ተደርጎላቸዋል፡፡
በተመሳሳይም በከተማው አረጋውያንን ጨምሮ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የምገባ ማእከል በቅርቡ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም ተገልጿል።
ማእከሉ በቀን ከ250 በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካማና ችግረኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ምግብ በነጻ በማቅረብ ማህበረሰባዊ አገልግሎቶችን እንደሚሰጥም በወቅቱ ተመላክቷል፡፡