የኢዜአ የቀድሞ ባልደረባ የነበሩት ጋዜጠኛ ግሩም ደጉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ - ኢዜአ አማርኛ
የኢዜአ የቀድሞ ባልደረባ የነበሩት ጋዜጠኛ ግሩም ደጉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 28/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በጋዜጠኝነት ያገለገሉት ግሩም ደጉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ጋዜጠኛ ግሩም ከአባታቸው አቶ ደጉ አበበ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ሀምሳለ የምሩ ሚያዝያ 2 ቀን 1950 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ መወለዳቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
በቤተሰባቸው አማካይነት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በወይዘሮ ቀለመወርቅ ጥሩነህ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በአርበኞች እንዲሁም በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተምረዋል።
ጋዜጠኛ ግሩም ከግንቦት 13 ቀን 1968 ዓ.ም ጀምሮ በቀድሞ ማስታወቂያ ሚኒስቴር በመቀጠር በጡረታ እስከተገለሉበት እስከ መስከረም 1 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ ለ40 አመታት በጋዜጠኝነት አገልግለዋል።
በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) ቆይታቸው በአሶሳ፣ ደብረ ብርሃንና ጅማ ቅርንጫፎች ሰርተዋል።
ጋዜጠኛ ግሩም ትናንት በ67 አመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን የቀብር ስነ ስርአታቸውም በአዲስ አበባ ላፍቶ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ተፈጽሟል።
ጋዜጠኛ ግሩም ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት ነበሩ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ይመኛል።