ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማንሳቱን አረጋገጠ 

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 28/2017 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2017 ዓ.ም ኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማንሳቱን ዛሬ አረጋግጧል።

በሃዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ በተደረገው የሊጉ የ25ኛ ሳምንት ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦሌ ክፍለ ከተማን 5 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።

ንግስት በቀለ ሶስት ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ ሀትሪክ ስትሰራ ሴናፍ ዋቁማ እና ረድኤት አስረሳኸኝ ቀሪዎቹን ጎሎች አስቆጥረዋል። 

ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ59 ነጥብ አንድ ጨዋታ እየቀረው የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን አረጋግጧል። 

ንግድ ባንክ የሊጉ አሸናፊ የሆነው በውድድር ዓመቱ ምንም ሽንፈት ሳያስተናግድ ነው።

ተከታዩ ሃዋሳ ከተማ በ50 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሊጉ የበላይ ሲሆን ይህ ለተከታታይ አምስተኛ በአጠቃላይ ለስምንተኛ ጊዜ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። 

ሴናፍ ዋቁማ በሊጉ ያስቆጠረቻቸውን ግቦች ወደ 21 ከፍ በማድረግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት መሪነቷን አጠናክራለች። 

የሃዋሳ ከተማዋ እሙሽ ዳንኤል በ13 ጎሎች ትከተላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም