ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ዕድገት የሚመጥንና ጠንካራ የሰላም ዘብ የሆነ የፖሊስ ሠራዊት እየገነባን ነው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ዕድገት የሚመጥንና ጠንካራ የሰላም ዘብ የሆነ የፖሊስ ሠራዊት እየገነባን ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በመሠረታዊ የፖሊስ ስልጠና ለ25ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ምልምል የፖሊስ አባላት አስመርቋል።


 

በምረቃ መርሃ-ግብሩ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በዘመናዊ መንገድ ፖሊስን ካዋቀረች 116ኛ ዓመታትን ማስቆጠሯን አውስተዋል።

ፖሊስ የሠላም ዘብ የልማትም ኃይል መሆኑንም ተናግረዋል።

ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች በሠላማዊና ህጋዊ መንገድ እንዲሳለጡ የፖሊስ ሚና አይተኬ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በተደመረ አቅም የብልፅግና ተምሳሌት የመሆን ራዕይዋ እንዲሳካ ሰላምና ህግን ማስከበር እንደሚገባም አስረድተዋል።


 

ፖሊስ የፀረ ሠላም ኃይሎችን እኩይ ተልዕኮ በማምከን፣ ኮንትሮባንድን፣ የኢኮኖሚ አሻጥርን፣ ደረቅ ወንጀልን፣ ማጭበርበርን፣ ሙስናን እና ገቢ ሥወራን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ጉልህ አበርክቶ እንዳለው አንስተዋል።

በሀገሪቱ ዕድገት ልክ በሥልጠና፣ በቴክኖሎጂ እና በመፈጸም ዐቅሙ የዳበረ የፖሊስ ሠራዊት እየተገነባ መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

መንግሥት ለፀጥታና ደህንነት ሪፎርም በሰጠው ትኩረት፥ ፖሊስን በቴክሎጂ ለማላቅ፣ በሥልጠና ለማዘመን እና የሥራ ቦታዎችን ምቹ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።


 

የዛሬ ተመራቂ ፖሊሶች የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ከሽብርተኞች፣ ከወንጀለኞች፣ ከባንዳዎች እና ከአሻጥረኞች የመጠበቅ ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዲወጡም አሳስበዋል።

ለዚህም የቆሙለትን ዓላማ ማወቅ፣ ሕግ ማክበር፣ ራሳቸውን በየጊዜው በፖሊሳዊ እውቀትና ክህሎት ማዳበር እንደሚጠበቅባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም