ኢትዮጵያን ከየትኛውም ፀረ ሰላም ኃይል የመጠበቅ ኃላፊነታችንን በብቃት እንወጣለን - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ከየትኛውም ፀረ ሰላም ኃይል የመጠበቅ ኃላፊነታችንን በብቃት እንወጣለን - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን ከየትኛውም ፀረ ሰላም ኃይል የመጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነታችንን በብቃት እንወጣለን ሲሉ ኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በተለያዩ መስኮች ያሰለጠናቸውን የ25ኛ ዙር ምልምል ፖሊሶች በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ አስመርቋል።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ባደረጉት ንግግር፥ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በለውጡ ዓመታት በጠንካራ ቁመና እየተገነባ ነው ብለዋል።
በተለይም ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እና ከብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጣ የፖሊስ ሠራዊትን በማደራጀት እውነተኛ ህብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊ የፖሊስ ተቋም ሆኖ መገንባቱን ገልጸዋል።
ፌዴራል ፖሊስ ኢትዮጵያን ከየትኛውም ጠላት የሚጠብቅ፣ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት የሚያረጋግጥ ግዙፍ የፀጥታ ኃይል መሆኑንም ተናግረዋል።
የዛሬ ተመራቂ ምልምል ፖሊሶችም ረጅም ጊዜ ወስደው በአስቸጋሪ የአየር ፀባይና መልክዓ ምድር ፈተናዎችን ያለፈ ስልጠና መከታተላቸውን አንስተዋል።
በዚህም ፖሊሳዊ ግዳጅን በብቃት መወጣት የሚያስችል ስልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
በተልዕኮ ስምሪታቸውም የውጭ ጠላቶችን ተልዕኮ ተቀብለው ሀገር ለማወክ በሚንቀሳቀሱ ፅንፈኞች ላይ ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የማያዳግም እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር ሁልጊዜም ከየትኛውም ፀረ ሰላም ኃይል መጠበቅ አንድነቷን የማፅናት ታሪካዊ ኃላፊነታችንን በብቃት እንወጣለን ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ፖሊስ የራሱ ቀይ መስመሮች አሉት ያሉት ኮሚሽነር ጀነራሉ፥ ከየትኛውም ዘር፣ ሃይማኖትና ፖለቲካ ሳይወግን ኢትዮጵያን ከጠላቶቿ ይጠብቃል ብለዋል።
ተመራቂዎችም ሀገራቸውን፣ ህዝባቸውንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን የመጠበቅ፣ ተልዕኳቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው በፖሊሳዊ ሙያ ክህሎትና ስነ-ምግባር የታነፁ የፖሊስ አባላትን ለማፍራት ተከታታይ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
የ25ኛ ዙር ምልምል ሠልጣኞችም የፖሊሳዊ ስነምግባር፣ የወንጀል መከላከል፣ የወንጀል ምርመራ፣ የፀረ ሽብር፣ የትራፊክ ፖሊስ፣ የህገመንግስትና ሌሎች የንድፈ ሀሳብ እንዲሁም ልዩ ልዩ የአካል ብቃት ሥልጠናዎችን መውሰዳቸውን አንስተዋል።
በስልጠና ብቁ መሆናቸው በየጊዜው በመመዘን ሀገርን ለማገልገል ያላቸው የዕውቀት፣ የክህሎትና ፖሊሳዊ ዲሲፕሊን ተፈትሾ ለምረቃ መብቃታቸውንም ገልጸዋል።