የኢትዮጵያና እስራኤል የንግድ ፎረም የሀገራቱን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የሚያጎለብት ነው - ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና እስራኤል የንግድ ፎረም የሀገራቱን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የሚያጎለብት ነው - ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና እስራኤል የንግድ ፎረም የሀገራቱን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የሚያጎለብት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ እስራኤል የንግድ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በመርሃ-ግብሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር)፣ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ሰአር፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሀም በላይ(ዶ/ር) በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አቭራሃም ንጉሴ (ዶ/ር) ፣ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የእስራኤል የቢዝነስ ልኡክና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፣ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመድረኩ ላይ መገኘት ኢትዮጵያ ለትብብር ኢንቨስትመንት እና እድገት ባላት ትልቅ አቅም ላይ ያለውን እምነት የሚያሳይ ነው።
በኢትዮጵያ እና በእስራኤል መካከል ያለው ግንኙነት ልዩ እና ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ መሆኑንም አንስተዋል።
ይህ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ግንኙነትም በግብርና፣ በውሃ አስተዳደር፣ በጤና፣ በቴክኖሎጂ እና በትምህርት ዘርፎች ላይ መስፋፋቱን ገልጸዋል።
መድረኩ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን የሚያጎለብት መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ሰአር እስራኤል የኢትዮጵያ የስኬቷ አካል መሆን ትፈልጋለች ብለዋል።
ከልዑካኑ መካከል የተወሰኑት እዚሁ በኢትዮጵያ የተወለዱ መሆናቸውን አንስተዋል።
የሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት ለኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸው መሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በኢትዮጵያ ጉብኝት በማድረግ ላይ ካሉት የእሥራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ሰአር ጋር በኢትዮ-እሥራኤል ግንኙነት ላይ በትላንትናው እለት መወያየታቸው ይታወሳል።
ሁለቱ ሀገራት በታሪክ ሥረ-መሠረት ላይ የተገነባ ረዥም ዘመን የቆየ ግንኙነታቸው ዛሬም መቀጠሉን እና ትብብሩ በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊ፣ በዲፕሎማሲያዊ፣ በማኅበራዊ እና በሌሎችም መስኮች ላይ ስለመጠናከሩ መግለጻቸውም እንዲሁ።