ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አገልግሎትን በማዘመን የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን እያሳደገ ነው -ሚኒስትር መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 28/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተቋማትን አገልግሎት በማዘመን የአምራች ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን እያሳደገ እንደሚገኝ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፥በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መርቀው የከፈቱት ሦስተኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ መካሄዱን ቀጥሏል።

አራተኛ ቀኑን በያዘው በዚሁ የኤክስፖም "በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተቋማዊና ቅንጅታዊ አሰራር የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ማሳደግ" በሚል መሪ ሀሳብ የፓናል ውይይት በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በፓናል ውይይቱም የፋይናንስ፣ጉምሩክ፣ቴክኖሎጂና ቢዝነስ ድጋፍ፣ አገልግሎቶችን በመስጠት የአምራች ዘርፉን አስተማማኝ የሎጂስቲክስ አገልግሎት በመስጠት የግብዓትና ሸቀጦች ፍሰት ማሳለጥ እንዲሁም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በመጠቀም የአምራች ዘርፉ የሚያጋጥሙትን ችግሮችን መፍታት የሚሉት ጉዳዮች ይዳሰሳሉ።

በመድረኩ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ፣ የጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አዘዘው ጫኔ፣የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ፣ የኢትዮጵያ ባሕርና ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመውን ጨምሮ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ተዋናይ የተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በዚሁ ጊዜ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፥ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለዘርፍ የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ወሳኝ ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል።

በፓናል ውይይትም አምራች ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ፍላጎትን ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አያና ዘውዴ (ዶ/ር)፥ንቅናቄው የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ለማሳለጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ባቀረቡት የመነሻ ጽሁፍ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር ውስጥ አልሚዎችን ማበረታታት፣ መሪ ኢንዱስትሪን መፍጠር፣ ለግሉ ዘርፍ ምቹ ከባቢን መፍጠር፣ ለአምራች ኢንዱስትሪ ችግር ፈች የምርምር ስራን ማከናወን፣ የኢንዱስትሪ ማኅበረሰብ መገንባት እና ሌሎች መሰረታዊ መሰሶዎችን የያዘ የ10 ዓመታት ጉዞ እንዳለው አስገንዝበዋል።

በዚህም የአጭር፣መካከለኛና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂክ ዕቅድ በመቅረጽ የተኪ ምርትና ወጪ ንግድን የሚያሳድጉ የኢንዱስትሪ ምርታማነትና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም