ቀጥታ፡

ኢ-ኮሜርስን ውጤታማ ማድረግ የሚያስችል የዲጂታል ክፍያ መሰረት ተጥሏል-የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 28/2017 (ኢዜአ)፦ኢ-ኮሜርስ (ኢሌክትሮኒክ ንግድ) ውጤታማ ማድረግ የሚያስችል የዲጂታል ክፍያ መሰረት መጣሉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን አስታወቁ፡፡

ኢ-ኮሜርስ ማለት በቀላሉ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በኢንተርኔት መግዛትና መሸጥ ማለት ነው።

ይህ በተለምዶ ሱቅ ከፍቶ ከመሸጥ ጋር ተመሳሳይነት ያለው የኦንላይን ስሪት ነው፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒሰትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፥ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የዓለማችን አገራት ኢ-ኮሜርስ የንግድ ስራቸውን እያከናወኑ ይገኛል፡።

አገራት ከስልሳ እስከ ዘጠና በመቶ ንግዳቸውን ኢ-ኮሜርስ የሚያደርጉ መሆኑን ገልጸው፤ የዓለም የንግድ ሁኔታ ካለ ኢ-ኮሜርስ ማሳለጥ ከባድ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ የኢ-ኮሜርስ ንግድን ዘርፉ ውጤታማ ለማድረግ አቅዳ እየሰራች መሆኑን አስታውቀዋል።

መንግስት ኢ-ኮሜርስ ተግባራዊ ለማድረግ ስትራቴጂ ነድፎ ወደ ስራ መግባቱን ለአብነት አንስተዋል፡፡

የዲጂታል ክፍያ ለኢ-ኮሜርስ ግብይት ለማከናወን ዋናው ነገር ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ኢትዮጵያ ዲጂታል ክፍያ መጀመሯ ለዚህ ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል።

በቴሌ ብር፣በሲቢ ብር እና ሌሎች አማራጮች የዲጂታል ክፍያዎች እየተከናወኑ መሆኑ ኢ-ኮሜርስ ውጤታማነት መሰረት የተጣለ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ኢ-ኮሜርስ ስርዓት ሲዘረጋ ለሸማቹ እንዲሁም ለነጋዴው ዘርፈ ብዙ ጥቅም ይሰጣል ብለዋል፡፡

በተለይ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ምርቶች በቀላሉ ወደ ተለያዩ አገራት እንዲደርሱ ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ዜጎች ቤታቸው ሆነው የፈለጉትን ግዢ የሚፈጽሙበት ምርት አቅራቢዎችም ምርታቸውን በቀላሉ እንዲሸጡ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም