የዲጂታል መረጃ ስርዓቱ የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል አቅም መገንባት ያስችላል- ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል መረጃ ስርዓቱ የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል አቅም መገንባት ያስችላል- ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 28/2017(ኢዜአ)፦ ለአርሶ አደሮች ስለ አየር ንብረት ሁኔታ መረጃ የሚሰጠው ዲጂታል ስርዓት የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል አቅም ለመገንባት ቁልፍ ሚና እንዳለው የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን (ዶ/ር) ገለጹ።
የመረጃ አገልግሎት ስርዓቱን ለመቋቋም የተዘጋጀ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ስብሰባ ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
ውይይቱ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) እና በምግብ ዋስትና ላይ የሚሰራው ዓለም አቀፍ ጥምረት (CGIAR) ስር ያለው የአየር ንብረት ምርምር ፕሮጀክት (AICCRA) በጋራ ያዘጋጁት ነው።
ስርዓቱ የተቀናጀ የአየር ንብረት ለውጥ መረጃን ከግብርና ዘርፍ ውሳኔ አሰጣጥ ጋር በማጣመር አርሶ አደሮች የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን መቋቋም የሚችሉበት አቅም መገንባትን አልሟል።
በሞባይል እና ድረ ገጽ አማራጭ የሚሰራው ይህ ስርዓት ለአርሶ አደሮች ዘር የሚዘሩበትን ወቅት፣ የሰብል አይነት መረጣ እና የምርት መሰብሰቢያ ጊዜን የተመለከቱ መረጃዎችን የአየር ትንበያ፣ የአየር ንብረት መረጃ እና የሰብል ባህሪያትን መሰረት በማድረግ የሚሰጥ ነው።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን (ዶ/ር) የዲጂታል ስርዓቱ የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎችን ከመቋቋም ባሻገር አስቀድሞ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል እንደሆነ ገልጸዋል።
የመረጃ ስርዓቱ የአፈር ጤና፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይገበር እና የካርቦን ልህቀትን በመቀነስ የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ የሚቻልበትን ዘዴ እና አቅም መገንባትን ጨምሮ በሌሎች ቁልፍ ጉዳዮች ላይ የእውቀት እና የመረጃ ልውውጥ ማድረግ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
የዲጂታል አሰራሩ የዘርፉ ተዋንያን የምግብ ዋስትት እና ዘላቂነትን አስመልክቶ ሙያዊ ምልከታቸውን የሚሰጡበትና መረጃ የሚያገኙበት ቋት እንደሆነም ነው ያስረዱት።
ስርዓቱን በተቀናጀ ሁኔታ በመጠቀም የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል በጋራ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የኢጋድ የከባቢ አየር እና የተፈጥሮ ሀብቶች ዳይሬክተር ዳሄር ኤልሚ ሁሴን በበኩላቸው፥ በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበረው ፕሮጀክት ለሰባት ዓመት እንደሚቆይ እና የምግብ ስርዓትን ለማጠናከር ወሳኝ አብክሮ እንዳለው ተናግረዋል።
በውይይቱ ላይ የዲጂታል ስርዓቱ ይፋ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የኢጋድ ተጠሪ አበባው ቢሆነኝ ኢጋድ የምግብ እና ስርዓተ ምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ፣ የዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ለመፍጠር እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብለዋል።
የአገልግሎቱ ይፋ መሆን የኢጋድ ትልዕኮን ለማሳካት እንደሚያግዝ አመልክተዋል።
ቀጣናዊው ስብስባ እስከ ሚያዚያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ የኢጋድ መረጃ ያመለክታል።