ቀጥታ፡

ከኢንተር ሚላን እና ባርሴሎና ማን ለፍጻሜ ያልፍ ይሆን?

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 28/2017(ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ኢንተር ሚላን  እና ባርሴሎና ዛሬ የሚያደርጉት የግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ እጅጉን ተጠባቂ ነው።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በሳን ሲሮ ስታዲየም ይካሄዳል።

ቡድኖቹ ባለፈው ሳምንት ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ሶስት አቻ ተለያይተዋል።

በጨዋታው ባርሴሎና ሁለት ጊዜ ከመመራት ተነስቶ አቻ መሆኑ አይዘነጋም።

በመጀመሪያው ዙር የታየው አዝናኝ ጨዋታ እና ጠንካራ ፉክክር የዛሬን ፍልሚያ ይበልጥ እንዲጠበቅ አድርጎታል።

በመልሱ ጨዋታ ኢንተር ሚላን ላሚን ያማልን ለማቆም፣ ባርሴሎና የቆመ ኳስ ድክመቱን አርሞ የመግባት እቅድ ይዘዋል።

የኢንተር ሚላኑ አሰልጣኝ ሲሞኒ ኢንዛጊ በ50 ዓመት አንዴ የሚገኝ ድንቅ ተጫዋች ያሉትን ያማልን ለማቆም አስቸጋሪ ቢሆንም ተጫዋቹ ኳስ እንዳይደርሰው የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን ብሏል።

በደጋፊያችን ፊት የምናደርገውን የፍጻሜ ጨዋታ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንግባለን ሲል ተናግሯል።

የባርሴሎናው አሰልጣኝ ሃንሲ ፍሊክ ጨዋታውን እንደ ፍጻሜ ጨዋታ አድርገን ነው የምናየው፤ ጨዋታውን ለማሸነፍ የሚጠበቅብንን ሁሉ እናደርጋለን ሲል ገልጿል።

በመጀመሪያው ዙር መከላከልን ጨምሮ የነበሩብን ድክመቶች ለማረም እንጥራለን ያለው አሰልጣኙ በተጫዋቾች አሰላለፍ ላይ ለውጥ እንደሚያደርግ ፍንጭ ሰጥቷል።

በኢንተር ሚላን በኩል ጉዳት አጋጥሞት የነበረው ላውታሮ ማርቲኔዝ በዛሬው ጨዋታ ላይ ሊሰለፍ እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል።

ሮበርት ሌዋንዶስኪ ከጉዳት ወደ ሜዳ መመለሱ ለባርሴሎና መልካም ዜና ሆኗል።

በሁለቱም በኩል የፍጻሜ ጨዋታ የሚል ስያሜ በተሰጠው ፍልሚያ ማን የዋንጫው ተፋላሚ ይሆናል? የሚለው ጉዳይ የተመልካችን ቀልብ የሳበ ሆኗል።

የ44 ዓመቱ ፖላንዳዊ ሲሞን ማርሲኒያክ ተጠባቂውን ፍልሚያ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም