ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና እስራኤል ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በትብብር ይሰራሉ - ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ ፤ ሚያዝያ 27/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና እስራኤል ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር በትብብር እንደሚሰሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ አዲስ አበባ የገቡትን የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዲዮን ሳር በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ውይይቱን አስመልክቶም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ፤ ሽብርተኝነት የሁለቱ አገራት ስጋት መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ለቀጣናው ሰላምና ለሁለቱ አገራት የጋራ ደህንነት ሲባል ሽብርተኝነትን በትብብር ለመመከት ተወያይተናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና እስራኤል የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ያላቸው ሀገሮች መሆናቸውን ገልጸው፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና የኢኮኖሚ ትብብርን ማጠናከር የሚያስችል የቢዝነስ ፎረም ነገ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

የቢዝነስ ፎረሙ የሁለቱን አገራት ሁለንተናዊ ትብብር በማጠናከር ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ውጤት ይገኝበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም አንስተዋል።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዲዮን ሳር በበኩላቸው በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ነው የጠቆሙት።

በአዲስ አበባ ለተደረገላቸው የሞቀ አቀባበልም ምስጋና አቅርበው፣ እንኳን ለአርበኞች የድል በዓል አደረሳችሁ ብለዋል።

ኢትዮጵያና እስራኤል ታሪካዊና ጥልቅ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተው፤ ሁለንተናዊ ትብብራቸውን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ እስራኤል በረራ በማድረግ ለሁለቱ አገራት ግንኙነት ገንቢ ሚና እንደሚጫወት ገልጸው፣ በግብርና፣ ቴክኖሎጂ፣ ንግድ፣ ጤናና መሰል ዘርፎች በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ መግቢያ የእስራኤል ጠቃሚ አጋር መሆኗን ጠቅሰው፤ ሽብርተኝነትን በመመከት ረገድም በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ባሳለፍነው መጋቢት 2017 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) በእስራኤል የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

በወቅቱም ከእስራኤል አቻቸው ጋር በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ጉዳዮች ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን በአገራቱ መካከል ያለውን ረጅም ዘመን ያስቆጠረ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከርም ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም