በእናቶችና ጨቅላ ህፃናት ጤና ክብካቤ አበረታች ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ደብረ ብርሃን ፤ሚያዝያ 27/2017(ኢዜአ)፦የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ ያስቻሉ አበረታች ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ዓለም አቀፍ የአዋላጅ ነርሶች(የሚድዋይፎች) ቀን "ሚድዋይፎች በማንኛውም የሰብአዊ ቀውስ ውስጥ ምላሽ ለመስጠት ሚናቸው ከፍተኛ ነው" በሚል ሃሳብ ለ34ኛ ጊዜ በደብረ ብርሃን ከተማ ዛሬ ተከብሯል።

በጤና ሚኒስቴር የብሄራዊ የእናቶች ጤና አስተባባሪ ሲስተር ዘምዘም መሐመድ በበዓሉ ላይ እንደገለጹት መንግስት የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ አበረታች ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

በዚህም በጤና ተቋማትና በሰለጠነ ባለሙያ የሚወልዱ እናቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰዋል ።


 

መንግስት የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ ለክልሎች የአምቡላንሶችና ሌሎች ድጋፎችንም እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል ።

በ185 ጤና ጣቢያዎች የቀዶ ህክምና አገልግሎት ማስጀመር መቻሉን ጠቁመው ዛሬ የተከበረው ዓለም አቀፍ የአዋላጅ ነርሶች ቀንም የባለሙያዎቹን ተነሳሽነት በማሳደግ አገልግሎቱን ለማሻሻል ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አዋላጅ ነርሶች ማህበር ምክትል ዳይሬክተር አቶ ኢብራሂም ይመር በበኩላቸው ማህበሩ የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ጤና ለማሻሻል የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ማህበሩ ከሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በስድስት ክልሎች የባለሙያዎችን አቅም በማሳደግና ቁሳቁስ በማቅረብ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ ፀዳለ ሰሙንጉስ እንደገለጹት በዞኑ የአዋላጅ ነርሶች ማህበር የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ አበርክቶው የላቀ ነው ።

በዞኑ 91 ጤና ተቋማት የእናቶች ማቆያ ማደራጀት መቻሉንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም