ጀግኖች አርበኞች በጀግንነት ያስረከቡንን ሀገር ትውልዱም በአንድነትና በትጋት እድገቷን ማረጋገጥ አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ጀግኖች አርበኞች በጀግንነት ያስረከቡንን ሀገር ትውልዱም በአንድነትና በትጋት እድገቷን ማረጋገጥ አለበት
ባህር ዳር/ደብረ ብርሃን፤ሚያዝያ 27/2017(ኢዜአ)፦ጀግኖች አርበኞች በፈጸሙት አኩሪ ተጋድሎ ያስረከቡንን ነጻ ሀገር የአሁኑ ትውልድ አንድነቱንና አብሮነቱን በማጠናከር ለቀጣይ ትውልድ የበለጸገች ሀገር ማስረከብ እንዳለበት ተገለጸ።
84ኛው የኢትዮጵያ አርበኞች ቀን በዓል በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና በደብረ ብርሃን ከተማ በፓናል ውይይትና በሌሎች ዝግጅቶች ተከብሯል።
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በነበረው ውይይት ላይ የአማራ ክልል ጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚደንት አቶ ዳኝነት አያሌው በወቅቱ እንዳሉት፥ ጀግኖች አርበኞች ነጻነቷን ጠብቀው ያስረከቡንን ሀገር "የአሁኑ ተውልድም ጠብቆ ከነክብሯ ለመጪው ትውልድ ማቆየት ይኖርበታል"።
ወራሪው ጠላት በወቅቱ የተለያዩ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ታጥቆ ለቅኝ ግዛት ቢመጣም በኢትዮጵያዊያን ጀግኖች አርበኞች አኩሪ ተጋድሎ ዕቅዱ መክሸፉን አስታውሰዋል።
የዛሬው ትውልድም አንድነቱንና አብሮነቱን ይበልጥ በማጠናከር የአባቶቹን አኩሪ ተጋድሎ ሀገርን በማልማትና ዕድገቷን በማፋጠን መድገም አለበት ሲሉም አስገንዝበዋል።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ስትራቴጂክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዘውዱ ዕምሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች አርበኞች የፈፀሙት አኩሪ ተጋድሎ ለመላ ጥቁር ህዝቦች ጽናትንና አይበገሬነትን አስተምሯል።
ቀኑ ሲዘከር ጀግኖች አርበኞች ዳር ድንበር ለማስከበር ያደረጉትን ተጋድሎና የከፈሉትን የህይወት መስዋዕትነት ጭምር በማስታወስ መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል።
በጀግኖች አርበኞች የተፈፀሙ አኩሪ ታሪኮችን በጥናትና በምርምር በማስደገፍ መጪው ትውልድ በሚገባ እንዲያውቀው ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የዩኒቨርሲቲው የሁለተኛ ዓመት የቪዥዋል አርት ዲፓርትመንት ተማሪ ኤርሚያስ ጥላሁን፣እስከ አፍንጫው የታጠቀን ጠላት የጥንት ጀግኖች አባቶችና እናቶች በጦርና በጎራዴ ድል ነስተው ያስረከቡን ነጻ ሀገር ከነክብሯ ማቆየት የእኛ የዛሬው ትውልድ ሃላፊነት ነው ብሏል።
ሰላሟና ልማቷ የተረጋገጠና የበለጸገች ሀገር ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ጠንክረን በመስራት የራሳችንን አዲስ ታሪክ መጻፍ ይኖርብናል ብሏል።
ከጀግኖች አርበኞች ተምረን በልማት ስኬታማ በመሆን ሀገርን ከድህነት ማላቀቅና የራሳችንን ዘመን ተሻጋሪ አዲስ ታሪክ መስራት አለብን ያለችው ደግሞ ሌላኛዋ የዩኒቨርሲቲው ተማሪ ሜሮን አወቀ ናት።
በዩኒቨርሲቲው የአባት አርበኞች ቀን ሲከበር የአማራ ክልል ጥንታዊት ጀግኖች አባት አርበኞች ማህበር አባላት እንዲሁም የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራን፣አመራሮችና ተማሪዎች ተገኝተዋል።
በተያያዘ ዜና በደብረ ብርሃን ከተማም 84ኛው የአርበኞች የድል መታሰቢያ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት የሰሜን ሸዋ ዞን የጀግኖች አርበኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ተክለስላሴ ከበደ እንደገለጹት፣ ጀግኖች አርበኞች በአንድነት በመቆም ሀገርን ከወራሪ ጠላት ታድገው ነጻ ሀገር ያስረከቡበት ምስጢር ለትውልዱ ትምህርት ነው።
የአርበኞችን የጀግንነት ታሪክ አጠናክሮ ለማስቀጠል የዛሬው ትውልድ ለሰላምና ለአብሮነቱ ተግቶ መስራት እንዳለበት የገለጹት፥ ደግሞ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አቶ አክሊል ጌታቸው ናቸው።
መምሪያው የተረከባቸውን ታሪካዊ ሥፍራዎች በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በማልማት ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ከጀግኖች አርበኞች ማህበር ጋር በመተባባር እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።