ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን እድገት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ባሉ ተግባር ሁሉም ተሳትፎውን ማጠናከር ይገባዋል-ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 27/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን እድገት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ውስጥ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በግዜ የለኝም መንፈስ ተሳትፎውን ማጠናከር እንዳለበት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በተገኙበት 84ኛው የአርበኞች የድል በዓል ተከብሯል።

በመርሀ-ግብሩ ላይም ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በአርበኞች መታሰቢያ ድል ሀውልት የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።

በመርሀ ግብሩ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ጨምሮ፣ የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አመራሮች እና አባላት፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ድሉ የፋሽዝምና ቅኝ ግዛት እሳቤ ዳግም እንዳያንሰራራ ያደረገ ነው ብለዋል።

የድሉ መከበር ትላንትን የሚያመላክት ዛሬን በከፍታ የሚመለከት እንዲሁም የነገን ጉዞ ጽናት አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከኢትዮጵያውያን አርበኞች የሀገር ፍቅር እና ለብሔራዊ ነጻነታችን ያለንን ቀናኢነት የምንማርበት መሆኑን አስገንዝበዋል።

እንዲሁም የሀገርን ታላቅነትን እና ይህንን አኩሪ የሀገር ፍቅር ለትውልድ ለማስተላለፍ ያለውን ጽኑ ፍቅር መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ እድገት እና ግስጋሴ የሚቆረቁራቸውን ድል እየነሳች ዛሬ ላይ መድረሷን ታሪክ የሚመሰክረው መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ ባለችበት የእድገት ደረጃ የምታጠፋው ጊዜ የላትም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ እያንዳንዱን ደቂቃ እና ሰዓት ለኢትዮጵያ ከፍታ በግዜ የለኝም መንፈስ መስራት የሁሉም ግዴታ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ እንድትራመድ ሰላሟ የጸና እንዲሆን በትጋት እያገለገሉ ያሉ የመከላከያ እና ሌሎች የጸጥታ ተቋማትም ሊመሰገኑ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም