ተቋሙ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ600 በላይ የመልካም አስተዳደር በደል ጥያቄ መዝገቦች ላይ ውሳኔ ሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
ተቋሙ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ600 በላይ የመልካም አስተዳደር በደል ጥያቄ መዝገቦች ላይ ውሳኔ ሰጥቷል
አዳማ፤ሚያዚያ 27/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ600 በላይ የመልካም አስተዳደር በደል ጥያቄ መዝገቦች ላይ ውሳኔ ማሰጠቱን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ስመኝ ውቤ፤ የተቋሙን አጠቃላይ ክንውን እና በተለይም በመልካም አስተዳደር የሚደርሱ በደሎችን በመቀበል እየተሰጠ ያለውን መፍትሄ አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ዋና እምባ ጠባቂዋ በማብራሪያቸው በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ለዋናው መስሪያ ቤትና በስምንት ቅርንጫፎቹ 1 ሺህ 700 አቤቱታዎች መቅረባቸውን አስታውሰዋል።
አቤቱታዎች የቀረቡት በአካል፣በፖስታ፣በስልክ ፣በጥሪ ማዕከል፣ በኢሜይል እና በሌሎችም አማራጮች መሆኑንም ጠቁመዋል።
በመሆኑም በዘጠኝ ወራት ከቀረቡት አቤቱታዎች መካከል ከ600 በላይ የመልካም አስተዳደር በደል ጥያቄ መዝገቦች ላይ ውሳኔ መሰጠቱን ገልጸዋል።
የይዞታ መብት ጥያቄ፣የካሳ ጥያቄ፣ከሥራ ያለአግባብ መባረር፣የጡረታ መብት አለማክበር እና ልዩ ልዩ ጉዳዮች እንደነበሩ አንስተው ጉዳዮቹ ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል ብለዋል።
የተወሰኑት አቤቱታዎች ደግሞ በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራትና በቀጣዩ ዓመት ምርመራ የሚካሄድባቸው ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።
ከተስተናገዱት አቤቱታዎች መካከል ከተቋሙ ስልጣንና ሃላፊነት ውጪ በሆኑት ላይ ደግሞ የሕግ ምክር በመስጠት የመፍትሄ አቅጣጫ የማመላከት ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።
ለተቋሙ የሚቀርቡ ጥቆማዎች ደረጃቸውን የጠበቁና በተቋሙ ስልጣን ስር የሚታዩ ብቻ እንዲሆኑ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።