የኢንቨስትመንትና የልማት ፕሮጀክቶች የአካባቢ ብክለትን መከላከል ታሳቢ ያደረገ የምርት ሂደት እንዲከተሉ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢንቨስትመንትና የልማት ፕሮጀክቶች የአካባቢ ብክለትን መከላከል ታሳቢ ያደረገ የምርት ሂደት እንዲከተሉ እየተደረገ ነው

አዳማ፤ ሚያዝያ 27/2017(ኢዜአ) - የኢንቨስትመንትና የልማት ፕሮጀክቶች የአካባቢ ብክለትን መከላከል ታሳቢ ያደረገ የምርት ሂደት እንዲከተሉ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር እያደረጉ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአማራ ክልልና የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የዘርፉ ሃላፊዎች ተናገሩ።
የአማራ ክልል የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን የአካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር አቶ አወቀ ይታይ፣ እንዳሉት ትራንስፖርት፣ የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርቶች፣ የድምፅና ሌሎች በካይ ነገሮች ለአካባቢ ብክለት ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ በርካታ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን ጠቅሰው እነዚህ የኢንቨስትመንትና የልማት ፕሮጀክቶች የአካባቢ ብክለትን ታሳቢ ያደረገ የምርት ሂደት እንዲከተሉ ክትትልና ቁጥጥር መጠናከሩን አስረድተዋል።
ችግሩን ለመቀነስም ለባለድርሻ አካላት ስልጠና መስጠትና ስለ ጉዳቱ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተከታታይ ግንዛቤ ማሳደጊያ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ኢንዱስትሪዎች ከግንዛቤ ባሻገር ብክለትን መቀነስ የሚያስችሉ አማራጭ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንዲችሉ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህም ባለፈ አሰራርና ተጠያቂነትን የሚያሰፍኑ የህግ ማዕቀፎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና የማስፈፀሚያ ስልቶች እየተዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የአከባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዳይሬክተር አቶ ደረጀ አቢቲ፤ በአስተዳደሩ የአካባቢ ድምፅና የውሃ አካላት ብክለት ቅድመ መከላከል ትኩረት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በተለይም ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ የልማት ፕሮጄክቶችና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ህገ እና ደንብ አክብረው እንዲሰሩ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በከተማው የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ጨምሮ ሌሎች የልማት ተቋማት የአካባቢ ብክለትን በሚቀንስ መልኩ የልማት ስራቸውን እንዲያከናውኑ በየጊዜው ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የእርምት እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም ገልጸዋል።
የድምፅና የውሃ አካላት ብክለት ለመከላከልም ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ የታዳሽ ሃይል በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል ድጋፍና የማበረታታት ስራዎች እንደሚሰሩም አስረድተዋል።
በተጨማሪም የከተማዋ የአረንጓዴ ልማት ስራ በተለይም በአፈርና ውሃ ዕቀባ፣ በደን ልማት እንዲሁም ከንኪኪ ነፃ አካባቢን በመፍጠር ረገድ በአስተዳድሩ የተሻለ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ጫናን ለመቋቋም የተናበበና የተቀናጀ ምላሽ ትግበራ ላይ ያተኮረ ውይይት ከሰሞኑ በአዳማ መካሄዱ ይታወሳል።