ቀጥታ፡

ወጣቱ ጀግኖች አባቶች በመስዋዕትነት ያስረከቡትን አገር ልማቷን በማረጋገጥ የዘመኑ አርበኛ መሆን አለበት

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 27/2017(ኢዜአ)፦ወጣቱ ጀግኖች አባቶች በመስዋዕትነት ያስረከቡትን አገር ልማቷን አጠናክሮ በማስቀጠል የዘመኑ አርበኛ መሆን እንደሚጠበቅበት የዘማች አርበኞች ቤተሰቦች ተናገሩ።

ኢትዮጵያ በየዘመኑ የገጠማትን የውጪ ጠላት በመመከት አኩሪና ደማቅ ታሪክን በመጻፍ ለትውልዱ ነጻና ሉአላዊ አገርን ያስረከቡ ቀደምት ጀግኖች ያሏት አገር ነች።

ከዚህ አልፎ የሌሎች ሀገራትን ሰላም ለማስጠበቅ በሔዱባቸው ሁሉ የአገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ በክብር ከፍ አድርገው የተጣለባቸውን ኃላፊነት በድል መወጣት የቻሉ መሆናቸውንም ታሪክ ያወሳዋል።

ዛሬ ለ84ኛ ጊዜ እየተከበረ ያለው የአርበኞች ቀን መታሰቢያ በዓል ይህንን አኩሪ ታሪክ ለትውልዱ ለማስተላለፍ እድል የሚፈጥር ነው።

በአሉን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአርበኞችና የዘማች ቤተሰቦች እንደገለጹት፥ የአገር ፍቅር በብዙ ተምሳሌታዊ ተግባር ይገለጻል።

ጀግኖች አባቶች ለአገራቸው መስዋዕትነትን የከፈሉት የተሻለች፣ ነጻነቷና ሉአላዊነቷ የተረጋገጠች አገርን ለትውልዱ ለማስተላለፍ መሆኑንም አክለዋል።

አገር በቅብብሎሽ የምትገነባ መሆኗን በመገንዘብና ለዚህም በመስራት ሰላሟና ልማቷ የተረጋገጠ አገርን ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው ብለዋል።

የዘማች ልጅ የሆነው አቶ ወንደሰን ማሞ እለቱን በማስመልክተ በሰጠው አስተያየት ከጀግኖች አባቶች የምንማረው በጦርነት ድል መንሳትን ብቻ ሳይሆን መተባበርንና አብሮነትን በመሆኑ ተናግረዋል።

ጀግኖች አባቶች ከራስ አልፎ ለሌሎች አገራት ሰላም መጠበቅ ዘብ በመቆምና በመሰል ጉዳዮች በዓለም አደባባይ የሚነገር ታሪክ ጽፈው ማለፋቸውንም ጠቅሰዋል።

የአሁኑ ትውልድም በልማት ስራ ላይ በጋራ መረባረብ እንዳለበት የሚያስተምር መሆኑንም ተናግረዋል።

ሌላው የዘማች አርበኛ ልጅ የሆኑት አቶ ኤፍሬም ኃይለማርያም በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ ጀግኖች የራሳቸውን አገር ሰላም ከማስጠበቅ በዘለለ ለተለያዩ አገራት ሰላም መረጋገጥ መስዋዕትነት ከፍለዋል።

በመስዋዕትነት ክብሯ ተጠብቆ የተረከብናትን አገር ልማቷን ማረጋገጥ ደግሞ የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነት ነው ብለዋል።

የአገር ፍቅርን በብዙ ተምሳሌታዊ ተግባር መግለጽ እንደሚቻል መማሯንና ልምድ መውሰዷን የተናገረችው ደግሞ ሌላዋ የኮሪያ ዘማች ልጅ እየሩሳሌም ከበደ ነች።

ቀደምት አባቶች አገርን ለመውረር የመጣውን ጠላት በመተባበር ድል ማድረጋቸውን በማንሳት፤ ወጣቱ የአገር ልማት በማፋጠን የራሱን ታሪክ መጻፍ እንዳለበት ነው የተናገረችው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም