በሐረሪ ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ መሻሻል ታይቷል - ተገልጋዮች - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ መሻሻል ታይቷል - ተገልጋዮች
ሐረር ፤ሚያዝያ 27/2017(ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ መሻሻል መታየቱን ተገልጋዮች ተናገሩ።
በቢሮው የተገኘው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተገልጋዮች እንዳሉት ቀደም ሲል ቢሮው ከመሬትና መሬት ነክ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የባለ ጉዳይ መጉላላት ይታይ እንደነበር አስታውሰዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የነበረው እንግልት በመቃለሉ መሻሻል ማሳየቱን ገልጸው፤ ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ከተገልጋዮች መካከል አቶ አማረ አለማየሁ በቅርቡ ከልማት ጋር በተያያዘ መኖሪያ ቤታቸው መፍረሱን ገልጸው፤ አሁን ግን አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ምትክ መሬት እንደተሰጣቸው አስረድተዋል።
ቢሮው ቀደም ሲል የነበሩበትን የአሰራር ችግሮች በመቅረፍ ለተገልጋዩ ማህበረሰብ እየሰጠ የሚገኘው ተግባር አበረታችና በቀጣይም ሊጠናከር እንደሚገባም አስተያየት ሰጥተዋል።
ቀደም ሲል ጉዳዮችን ለማስፈፀም ወደ ተቋሙ በሚመጡበት ወቅት መጉላላትና ምልልስ ይበዛው እንደነበር ያስታወሱት ደግሞ ወይዘሮ ፍሪ ሞገስ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ግን ይታዩ የነበሩ ችግሮች መቀረፋቸውን ገልጸው፤ በተለይ የተቋሙ የተለያዩ የስራ ክፍል ሃላፊዎች በሰዓቱ ወደ ቢሯቸው እንደሚገቡና ተገልጋዩንም በአግባቡ እንደሚያስተናግዱ ገልጸዋል።
መምህርት እሌኒ እሸቱ በበኩላቸው ቀደም ሲል በተቋሙ የስራ ሰዓትን አክብሮ ለተገልጋዩ ቀልጣፋ አገልግሎት የመስጠት ሁኔታ ውስንነት ይታይበት እንደነበር ገልጸው፤ አሁን ግን የስራ ሰዓትን አክብሮ ከመገኘት አንጻር መሻሻሎች ታይተዋል ብለዋል።
ለአንድ ጉዳይ የነበረው መመላለስም እየተቀረፈ እንደሚገኝ የጠቆሙት መምህርት እሌኒ ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የሐረሪ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ እንደሚሉት በቢሮው ቀደም ሲል ከመልካም አስተዳደርና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ውስንነቶች ነበሩ።
በዚህም የሪፎርም ስራዎችን በማከናወን በቢሮ ውስጥ የሚስተዋሉና ለተገልጋዩ እንቅፋት የሆኑ ውስንነቶችን የመቅረፍ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በቢሮው የተጀመሩ ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደትን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ አሰራሮችን በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
ይህም ከአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከፋይል መሰወር፣ ከብልሹ አሰራሮችና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚስተዋለውን ክፍተት እንደሚያቃልልም ገልጸዋል።