የካፒታል ገበያ ለአምራች ኢንዱስትሪው አማራጭ የፋይናንስ እድሎችን አቅርቧል - ኢዜአ አማርኛ
የካፒታል ገበያ ለአምራች ኢንዱስትሪው አማራጭ የፋይናንስ እድሎችን አቅርቧል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 27/2017(ኢዜአ)፦የካፒታል ገበያ ለአምራች ኢንዱስትሪው አማራጭ የፋይናንስ እድሎችን ማቅረቡን የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልቁ ገለጹ ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሦስተኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በይፋ መርቀው መክፈታቸው ይታወሳል ።
የኤክስፖው አካል የሆነ የፓናል ውይይት "የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዘመን እድሎችና ተግዳሮቶች" በሚል መሪ ሀሳብ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልቁ በመድረኩ እንደገለጹት፤ የካፒታል ገበያ ለተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና ለአገር በቀል ምጣኔ ሃብት ትልቅ ሚና ይጫወታል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ለምጣኔ ሃብት ሽግግር ቁልፍ ሚና ለሚጫወተው ኢንዱስትሪ የተለያዩ የፋይናንስ አማራጮችን ማቅረቡን ገልጸዋል።
ባለስልጣኑ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ የፋይናንስ አቅርቦት ለአምራች ኢንዱስትሪው ከሚያቀርበው አዲስ የፋይናንስ አማራጭ ውስጥ እንደሚካተት ጠቅሰዋል።
እንደ ዋና ዳሬክተሯ ገለጻ አምራች ኢንዱስትሪውን የሚደግፉ መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት በተለያዩ ቦንዶች አማካኝነት የፋይናንስ አማራጮችን ያቀርባል።
አነስተኛና መካከለኛ አምራቾችን በዘላቂነት ውጤታማ ለማድረግ የፋይናንስ ምንጫቸውን የሚያሰፉበት አማራጭ ባለስልጣኑ ዘርግቷል ነው ያሉት።
የካፒታል ገበያ ባለስልጣን የአምራች ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ የህግ ማዕቀፎችን ተግባራዊ ማድረጉን ጠቁመው አምራቾች የተፈጠረውን አዲስ የፋይናንስ አማራጭ መጠቀም እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የካፒታል ገበያ ከውጭ ባለሃብቶች ጋር ትብብርን በማጠናከር የፋይናንስ ምንጭን በማሳደግ በኩልም ጠቀሜታውን አስረድተዋል።
በምጣኔ ሃብት እድገት ውስጥ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማሳደግ አካታች ልማትን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ዘርፉን በመደገፍ ባለስልጣኑ የበኩሉን እንደሚወጣ ዋና ዳሬክተሯ አረጋግጠዋል።