ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ትውልድ ተሻጋሪ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 27/2017(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ትውልድ ተሻጋሪ መሆናቸውን ነዋሪዎች ገለጹ።

በኮሪደር ልማቱ እየፈካች የምትገኘው አዲስ አበባ ከልማቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ማግኘት ጀምራለች፡፡

የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ልዩ ገጽታ ከማጎናጸፉ በተጨማሪ ለቱሪዝም ምቹ የሆኑ አዳዲስ የጉብኝት መዳረሻዎችን በማካተት ነዋሪዎቿ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል።

መንግስት ከተማዋን የሚመጥኑ በርካታ የልማት ፕሮግራሞችን ነድፎ ባከናወናቸው ተግባራትም ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡


 

የፒያሳ፣ የአራት ኪሎ፣ የመገናኛ፣ የሜክሲኮ፣ የካዛችስ እና የቦሌ የኮሪደር ልማቶች ደግሞ የከተማዋን ስምና ግብር ያጣጣሙ ሌሎች አበይት የልማት ስራዎች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በተለይ ከለውጡ ወዲህ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን አስመልክቶ ከነዋሪዎች ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

በቆይታው ካነጋገራቸው ነዋሪዎች መካከል አሊ ኢማም እንዳሉት፤ በመዲናዋ የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እና የከተማዋን ገጽታ የሚቀይሩ በርካታ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል፡፡


 

በመከናወን ላይ ያሉ የልማት ስራዎች ህጻናትን፣ ወጣቶችንና አዋቂዎችን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸው ለየት እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል፡፡

የልማት ስራዎቹ ዘመናዊ የሆኑ፣ ጊዜውን የሚዋጁ እና ቀጣዩን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውንም ተመልክቻለሁ ብለዋል።

አቶ ገቢቴ ገነሞ በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ ከተማ በመከናወን ላይ ያሉ ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ለመጪው ትውልድ የሚሻገርሩ ናቸው ብለዋል፡፡

የስራ ባህል ለውጧል፣ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚቻልም ትምህርት ሰጥቷል ነው ያሉት።

በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ የተከናወነው የልማት ስራ ለመጭው ትውልድ ወረት ከመሆን ባለፈ አዳዲስ ነገሮችን እንዲፈጥሩ የሚያነሳሱ ናቸው ያሉት ደግሞ አሕመድ መሐመድ ናቸው፡፡

አቶ ዮናስ ወልደየሱስ በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማቱ ከፍተኛ የፕሮጀክት አፈጻጸም የታየበት እና ለሌሎች ክልሎች መነቃቃትን የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

ከሌሎች ተቋማት ጋር የነበረው ቅንጅት የሚደነቅ ነው ያሉት ዮናስ ልማቱ ለመጪው ትውልድ ጭምር በመሆኑ እንደራሳችን ሃብት ልንጠብቀው እና ልንንከባከበው ይገባል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም