ለኢንቨስተሮች ምቹ የኢንቨስትመንት አካባቢዎችን የመፍጠር ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ለኢንቨስተሮች ምቹ የኢንቨስትመንት አካባቢዎችን የመፍጠር ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 27/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ያለውን እምቅ አቅም ለኢንቨስተሮች ከማስተዋወቅ ባለፈ የተረጋጋ ምቹ የኢንቨስትመንት አካባቢዎችን የመፍጠር ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ገለጹ።
ሶስተኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በሁለተኛ ቀን ውሎው "የአምራች ኢንዱስትሪውን ዓለም አቀፍ የኤክስፖርት ገበያ መዳረሻ አማራጮችን ማስፋትና ዓለም አቀፍ የንግድ ስርዓቶችን መቀላቀል" በሚል መሪ ሃሳብ የፓናል ውይይት ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማጎልበት አገሪቷ ያላትን እምቅ አቅም ወደ ውጤት ለመቀየር እየሰራች ነው።
ለውጭ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ሀብት ከማስተዋወቅ ባሻገር ምቹ የኢንቨስትመንት አካባቢን ለመፍጠር ከሚመለከታቸው የዘርፉ ተዋናዮች ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብና የኤክስፖርት ዘርፉን ለማጎልበት አስቻይ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ አኳያ ኮሚሽኑ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ከሎጂስቲክ ጋር ተያይዞ መሰራት ያለባቸውን ስራዎች ከሚመለከታቸው የዘርፉ ተዋናዮች ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የመንግስትና የግሉን ዘርፍ ወደ አንድ መድረክ በማምጣት በኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚስችል ስራ እየተከናወነ መሆኑን አክለዋል።
ባለሃብቶች ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች አንዱ በሚፈለገው ልክ የገበያ መዳረሻ ማግኘት መሆኑን ጠቅሰው፤ ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ ምርቶችን የሚገዙ ድርጅቶችን ከባለሀብቶች ጋር በማስተሳሰር ኤክስፖርትን ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ በትኩረት እየሰራባቸው ካሉ ዐበይት ተግባራት መካከል የውጭ ኢንቨስትመንትን የመሳብና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በዘርፉ ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ አንዱ መሆኑንም ነው የገለጹት።
አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ ከሶስት ሺህ በላይ ድርጅቶችን በመለየት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል።