ኢትዮጵያ የወጪ ንግድን ለማሳደግ ለገበያ መዳረሻዎች ትኩረት ሰጥታለች - ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የወጪ ንግድን ለማሳደግ ለገበያ መዳረሻዎች ትኩረት ሰጥታለች - ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 27/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የወጪ ንግድን ለማሳደግ ለአህጉራዊና አለም አቀፍ የገበያ መዳረሻዎች ትኩረት መስጠቷን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።
የሦስተኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ አካል የሆነው የፓናል ውይይት "የአምራች ኢንዱስትሪው አለም አቀፍ የኤክስፖርት ገበያ መዳረሻ አማራጮችን ማስፋትና አለም አቀፍ የንግድ ስርዓቶችን መቀላቀል" በሚል መሪ ቃል ተካሂዷል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የወጪ ንግድን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች።
ለምርት ጥራት አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን ማሟላት፣ የወጪ ንግድ ማስተዋወቅና የገበያ መዳረሻን ማስፋት ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት ውስጥ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የገበያ መዳረሻን ከማስፋት አኳያ በሁለትዮሸና በባለ ብዙ ወገን፣ በአህጉራዊ እንዲሁም የአለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየተከናወነ ያለውን ተግባርም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያከናወነች ባለው ተግባር አምስት የድርድር ሂደቶችን ማለፍ የቻለች ሲሆን በቀጣይም የአገርን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የገለጹት።
በአፍሪካ አገራት መካከል የንግድ ልውውጥን ለማሳደግ 52 አገራት የፈረሙትን አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና የሙከራ ንግድ ለማድረግ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
ነጻ የንግድ ቀጣናው ከ3 ትርሊዮን ዶላር በላይ የሚንቀሳቀስበት በመሆኑ ለአምራች ዘርፉ ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱንም ጠቁመዋል።
በሳይንስና ቴክኖሎጂ በመታገዝ ለምርት መለያ (ብራንድ) ልማት ትኩረት በመስጠት በአለም አቀፍ ደረጃ የገበያ ተደራሽነትን ለማስፋት ወሳኝ መሆኑንም አመላክተዋል።