ካውንስሉ ወጣቶች ለአገራዊ ዕድገትና ልማት የሚኖራቸውን ሚና ለመወጣት የሚያስችላቸው ነው - ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ - ኢዜአ አማርኛ
ካውንስሉ ወጣቶች ለአገራዊ ዕድገትና ልማት የሚኖራቸውን ሚና ለመወጣት የሚያስችላቸው ነው - ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 26/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ወጣቶች ለአገራዊ ዕድገትና ልማት የሚኖራቸውን ሚና ለመወጣት የሚያስችላቸው መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ዛሬ ተመስርቷል።
በመርሀ-ግብሩ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋን ጨምሮ ከተለያዩ አካባቢዎቸ ዑለማዎች፣ የመጅሊስ አመራር አባላት እንዲሁም ወጣቶችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ በወቅቱ እንዳሉት ፤ ወጣቶች ለአገር ሰላም፣ ልማት እና እድገት መትጋት አለባቸው።
ወጣቶች ሀገርን የማሻገር ሀላፊነት እንደተጣለባቸው ገልጸው፤ ለዚህም ጠንክረው መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
የኢትየጵያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስልም በይፋ መመስረቱን አብስረዋል።
ካውንስሉ ወጣቶች ለአገራዊ ዕድገትና ልማት የሚኖራቸውን ሚና ለመወጣት የሚያስችላቸው መሆኑንም አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ሀላፊ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በበኩላቸው፤ አገርን ማሻገር የሚችሉ ወጣቶች ለተቋም ግንባታ ወሳኝ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ወጣቶች በሰላም በልማት እንዲሁም በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ሚናውን መወጣት የሚያስችለው መሆኑንም ተናግረዋል።
የወጣቶችን ሚና የሚያጠናክሩ ሰፋፊ ስራዎች መከናወናቸውን የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሱልጣን አማን ኤባ ናቸው።
ወጣቶች የብሩህ አእምሮ የእምቅ አቅም ባለቤት መሆናቸውን ገልጸዋል።
ወጣቶች በአገርና ህዝብ የተጣለባቸው ሀላፊነት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም አዎንታዊ ዝግጅት ሊኖራቸው እንደሚገባ አመልክተዋል።
ካውንስሉ ወጣቶች ሚናቸውን እንዲወጡ የሚያስችላቸው መሆኑን ገልጸው፤ ይህንን እውን ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ፕሬዝዳንት ኡስታዝ ሀይደር ኸድርም በበኩሉ፥ በቀጣይ ወጣቶች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ሚናቸውን የሚያጎለብቱበት ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቁሟል።
ወጣቱ በሰላም፣በልማት እንዲሁም በበጎ ፈቃድ ስራዎች የሚጠበቅበትን ሚና እንደሚወጣ አረጋግጧል።