መንግስት የኢንዱስትሪ ዘርፍ ተወዳዳሪና ውጤታማ እንዲሆን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የኢንዱስትሪ ዘርፍ ተወዳዳሪና ውጤታማ እንዲሆን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 26/2017(ኢዜአ)፦መንግስት አምራች ኢንዳስትሪው ተወዳዳሪና ውጤታማ እንዲሆን የሚያደርገውን ድጋፍና የቅንጅት ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ።
የሦስተኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ አካል የሆነው የፓናል ውይይት "የአምራች ኢንዱስትሪው አለም አቀፍ የኤክስፖርት ገበያ መዳረሻ አማራጮችን ማስፋትና አለም አቀፍ የንግድ ስርዓቶችን መቀላቀል" በሚል ርዕስ ተካሂዷል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የአገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶችን በመፍታት ውጤታማ እንዲሆኑ ኢትዮጵያ ታምርት አክስፖ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው አንስተዋል።
ዘርፉን ይበልጥ ለማስፋትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማጉላት የግሉን ዘርፍ ያማከሉ ተግባራትን ከማከናወን ባሻገር የአሰራር ስርዓቶችን ማዘመንና ማሻሻል ላይ ትኩረት መሰጠቱንም ገልጸዋል።
ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እና ተቀባይነት እንዲኖራቸው መዳረሻዎቻቸው የሚፈልጉትን የጥራት መስፈርት አሟልተው ሊገኙ ይገባል ብለዋል።
መንግስት አምራች ኢንዱስትሪው ተወዳዳሪና ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያደርገውን ድጋፍና የቅንጅት ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን በበኩላቸው፥ሚኒስቴሩ ከወጪ ንግድ ገበያው ጋር በተያያዘ ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየሰራች መሆኗን ገልፀው፤ ይህም በቀጣይ የኢትዮጵያን ምርት በተለያዩ አገራት ለማስፋት ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ውጤታማ የማድረግ እና ምቹ የኢንቨስትመንት አካባቢን የመፍጠር ስራ ከሚመለከታቸው የዘርፉ ተዋናዮች ጋር እየተሰራ ነው።
ለዚህም ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ ባለሀብቶች ለመሳብ እና የወጪ ንግድ ዘርፉን ለማጎልበት የተረጋጋ የኢንቨትመንትና የኢንዱስትሪ ተግባራት የሚያከናወኑበትን አስቻይ ሁኔታን የመፍጠር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ አኳያ ኮሚሽኑ በዘርፉ ላይ ኢንቨስተሮችን ለማሳብ ከሎጂስቲክስ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ተግባራት በቅንጅት እየተከናወኑ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሰረት በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ የወጪ ንግድ ምርቶች ጥራትና ደረጃቸው የጠበቁ እንዲሆኑ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
እንዲሁም የአገር ውስጥ ምርቶች ደረጃ እንዲወጣላቸው በማድረግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በመድረክ ከተገኙ የግል ዘርፉ አምራች ኢዱስትሪ ወክለው ከቀረቡት መካከል የደስታ ጋርመንት ስራ አስፈፃሚ እዮብ በቀለ ከመንግስት የተደረገላቸው ድጋፍ ለድርጅታቸው ውጤታማነት ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል።
አንድ ድርጅት ዓለም አቀፍ መለኪያዎች አሟልቶ ከተገኘ ዓለም አቀፍ ገበያውን ሰብሮ ገብቶ ውጤታማ የማይሆንበት ምክንያት የለም ብለዋል።
የኢትዮጵያ የላኪዎች ማህበር ስራ አስፈፃሚ ራሄል ሞገስ፥መሰል መድረኮች አምራች ኢንዳስትሪው ያሉባቸውን ችግሮች በማቃለል ውጤታማ እንዲሆን ያግዛል ብለዋል።
አንድን ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ለማግኘት የጥራት ቁጥጥር ማረጋገጫ ማግኘትና ለተጠቀሚው አመቺ በሆነ መንገድ ማዘጋጀት አስፈላጊነት አንስተዋል።