ቀጥታ፡

የመላው ኦሮሚያ ስፖርታዊ ጨዋታዎች ውድድር ጀመረ

አምቦ፤ሚያዚያ 26/2017(ኢዜአ)፦27ኛው መላው ኦሮሚያ ስፖርታዊ ጨዋታዎች ውድድር በአምቦ ከተማ መካሄድ ጀመረ።

በውድድሩ መክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሀመድ፣በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ሳዳት ነሻ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ፣ ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ እና ሌሎች የፌዴራልና የክልል የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መኪዩ ሞሃመድ እንደገለጽት፥ ስፖርት አብሮነትን ከማጠናከር ባለፈ ለአካልና ለአዕምሮ ጤና እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው።

ከዚህም ባለፈ ስፖርታዊ ውድድሮች በህዝቦች መካከል ትስስርን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላም ግንባታም ትልቅ ጠቀሜታ እንዳላቸው ገልጸዋል።

በምትክል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ሳዳት ነሻ፣የክልሉ መንግስት ስፖርታዊ እንቅስቃሴን በማጠናከር ውጤታማ ዜጋ ለማፍራት ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል።

በእስካሁኑ ሂደትም ተተኪ ስፖርተኛች በብዛት ማፍራት እንደተቻለ ተናግረው በቀጣይም በስፖርቱ ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማግኘት በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የስፖርት መሰረተ ልማት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ሰፋፊ ስራዎች እንደሚሰሩ አመላክተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጥላሁን፣ የመላ ኦሮሚያ ስፖርታዊ ጨዋታዎች ውድድር የተለያዩ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከነዚህም መካከል የተሻለ ብቃት ያላቸው ስፖርተኞችን ማፍራት፣ ስፖርታዊ ክህሎትና እውቀት ማጎልበት እንዲሁም ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ባህል ማድረግ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የከተማው ነዋሪ የውድድሩ ተሳታፊዎችን ተቀብሎ እያስተናገደ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአምቦ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃጫሉ ገመቹ ናቸው።

ወደ ከተማችን የመጣችሁ እንግዶችም የተሻለ ግዜ እንድታሳልፉ እመኛለሁ ብለዋል።

ዛሬ በአምቦ ከተማ በተጀመረው በመላው ኦሮሚያ ስፖርታዊ ጨዋታዎች ውድድር ከ8 ሺህ 500 በላይ ስፖርተኞች በ24 ዘመናዊ የስፖርት አይነቶች የሚሳተፉ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም