ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለ84ኛው የዐርበኞች (የድል) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 26/2017(ኢዜአ)፦ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለ84ኛው የዐርበኞች (የድል) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፥ ቀደምት እናትና አባቶቻችን ነጻነትን በደም አስከብረው ሀገር አውርሰውናል፤በዚህም እንኮራለን ነው ያሉት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት።

እነዚህ ቀደምት ዐርበኞች በከፈሉት ዋጋ ዛሬ ቀና ብለን በነጻነት ዐደባባይ እንድንራመድ አድርገውናል። በድህነታችንና በኋላ ቀርነታችን ምክንያት ግን ነጻነታችን ሙሉ ሊሆን አልቻለም ብለዋል።

ነጻነታችን የተሟላ እንዲሆን ዛሬ ኢትዮጵያ የሁለተኛውን ዘመን ዐርበኞች ትፈልጋለች ያሉ ሲሆን የሁለተኛው ዘመን ዐርበኞች ኢትዮጵያን ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና በማድረስ ነጻነቷን ሙሉ የሚያደርጉ ናቸው በማለት ገልጸዋል።

በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በማኅበራዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መስኮች በሚኖረው ሰላማዊ ጦርነት፣ ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ታግለው የሚያሸንፉ ዐርበኞች ናቸው።

የዚህ ዘመን ዐርበኝነት ትጥቁ ዕውቀት፣ ክህሎት እና ዲሲፕሊን ነው። ወኔው የሀገር ፍቅር፣ ቆራጥነት እና ንጽሕና ነው። ግቡ የኢትዮጵያ ብልጽግና ነው።

ኢትዮጵያን ታላቅ ለማድረግ ሁለቱም ዓይነት ዐርበኞች ያስፈልጋሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህ ዘመን ደግሞ ይበልጥ ሁለተኛውን አርበኝነት ይሻል ብለዋል።

ይሄ ቀን የመጀመሪያውን ዐርበኝነት መዘከሪያ፤ ለሁለተኛው ዐርበኝነት ደግሞ መሰረት ማፅኛ እንደሚሆን ተስፋዬ የላቀ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም