ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት መርሀግብር የኢትዮጵያን እድገት የሚያረጋግጡ ትላልቅ ተግባራት እየተከናወኑበት ነው -ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 26/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ታምርት መርሃግብር የኢትዮጵያን እድገት የሚያረጋግጡ ትላልቅ ተግባራት እየተከናወኑበት ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፥ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ የሚገኘውን የኢትየጵያ ታምርት ኤክስፖ ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እና የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር አረጋ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የግብርና ግብዓት የሚያቀነባብሩ፣ የማዕድን ምርት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች የሰውን እንቅስቃሴ የሚያቀላጥፉ ማሽኖች እና ሌሎች ተግባራትን ተመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በርካታ አስደናቂ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን እንደተመለከቱ ገልጸዋል።

በተለይ የኢትዮጵያን እድገት የሚያረጋግጡ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ግዙፍ ስራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል፡፡

በኢትየጵያ ታምርት መርሃግብር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት በኤክስፖ መቅረቡ ዜጎችን በማነቃቃትና አምራቾችን በማበረታታት በኩል ትልቅ ሚና የሚጫወቱ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡

የአገርን እድገት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ መሆኑን ጠቁመው፥ የኢትየጵያ ታምርት ኤክስፖ ትልቅ ትርጉም ያለው እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የሚካሔደውን ሦስተኛው የኢትየጵያ ኤክስፖ ትናንት መርቀው መክፈታቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም