ቀጥታ፡

ትውልዱ ጠንካራ የስራ ባሕል በመላበስ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት የተረጋገጠባት አገር የመገንባት ሂደቱን ማፋጠን አለበት

መቱ፤ሚያዝያ 26/2017 (ኢዜአ)፦ትውልዱ ጠንካራ የስራ ባሕል በመላበስ ኢኮኖሚ ሉዓላዊነት የተረጋገጠባት አገር የመገንባት ሂደቱን ማፋጠን እንዳለበት ተገለጸ።

84ኛ ዓመት የ'ሳምቤ' ድል መታሰቢያ የተለያዩ አካላት በተገኙበት በፓናል ውይይት በኢሉአባቦር መቱ ከተማ ተካሄዷል።

የጣሊያን ወረሪ ሃይል ለዳግም ወራረ በመጣበት ወቅት በምዕራቡ የኢትዮጵያ ክፍል ጎሬ ከተማን ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረት በኢትዮጵያውያን አንድነትና ጀግንነት በሳምቤ ተራራ ላይ በመክሸፉ ድሉም የ'ሳምቤ' ድል በመባል ይታወቃል።

በፓናል ውይይቱ ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የኢሉአባቦር ዞን ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ደበላ፣ በጦርነቱ ኢትዮጵያዊያን ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ ተሳትፈው ድል መጎናጸፋቸውን ገልጸዋል።

ጀግኖች አባቶች በጠንካራ አንድነታቸው ሉዓላዊነቷና ነጻነቷ የተጠበቀ አገር ለትውልድ ማቆየት መቻላቸውን ገልጸው፤ የአሁኑ ትውልድም አንድነትና ሕብረቱን በማጠናከር ድሕነትን ለማሸነፍ መነሳት አለበት ብለዋል።

የኢሉባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ በበኩላቸው፥ የዛሬው ትውልድ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠ አገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ንቁ ተሳታፊ መሆን ይገባል ብለዋል።

''የ'ሳምቤ' ድል መታሰቢያ በዓል ስናከብር ትውልዱ ስለ ሉዓላዊነትና ጀግንነት እንዲያውቅ፣የአባቶችን የድል ምስጢር እንዲረዳ ለማስቻል ነው ብለዋል።

ወጣቱ ትውልድ በአገር ግንባታ ሂደት በአንድነት በመቆም ሰላምና ልማትን በማረጋገጥ የድርሻውን እንዲወጣም የዞኑ አስተዳደር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ከኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ በፓናል ውይይቱ ላይ የተገኙት አቶ አድማሱ ዋቅጋሪ፣ ቀደምት አባቶች በጠንካራ የውስጥ አንድነታቸው ድል መቀዳጀታቸውን ገልጸው፤ይህም ለዛሬ ትውልድ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል።

አሁንም ብልጽግናችንን እውን ለማድረግ ያሉንን እምቅ ሀብቶችን በአግባቡ በማልማት የልማት ግባችንን ማሳካት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።

የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎችም በአንድነት በልማት ላይ በመሰማራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን ማሳደግ አለብን ብለዋል።

የ'ሳምቤ' ድል መታሰቢያ በዓሉ አከባበር ነገም ሲቀጥል ከአጎራባች ክልሎች የሚመጡ እንግዶች የሚሳተፉበት መድረክና የድሉ ስፍራ ጉብኝት የሚካሄድ መሆኑን ከወጣው መርሐ ግብር መረዳት ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም