የኤሌክትሪክ ተደራሸነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሪክ ተደራሸነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ሀዋሳ፤ሚያዝያ 26/2017 (ኢዜአ)፦በታዳሽ የሃይል አማራጭ ላይ መሰረት በማድረግ የኤሌክትሪክ ተደራሸነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ "የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክና ብርሃን ተደራሽነት" ፕሮጀክት አፈጻጻም ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት ውይይት በሀዋሳ እያካሄደ ነው፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢኒጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ባለፉት ሁለት ዓመታት በሀገሪቷ ያለውን ታዳሽ የሃይል አማራጭ ለመጠቀም የሚያስችል የፖሊሲ ማሻሻያ ተደርጎ ወደ ትግበራ ተገብቷል፡፡
ፖሊሲው የግል ባለሃብቶች ጭምር በዘርፉ እንዲሰማሩ እድል የሚፈጥርና በታዳሽ የሃይል አማራጭ ያሉንን ሀብቶች በተገቢው መጠቀም የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ብሔራዊ የኤክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ተቀርጾ ተግባራዊ መደረጉን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ፕሮግራሙ በዋናው የኤሌክትሪክ መስመርና በታዳሽ የሃይል አማራጭ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
ለፕሮግራሙ ከስድስት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን መንግስት ከዓለም ባንክና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር ለፕሮግራሙ ውጤታማነት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በፕሮግራሙ በታቀፈው "የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክና ብርሃን ተደራሽነት" ፕሮጀክት መሰረት ከዋና የኤሌክትሪክ መስመር ውጭ የሆኑ የገጠር አካባቢዎችን ለመድረስ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ከ240 ሺህ በላይ የቤተሰብ አባላትንና ከ1ሺህ 400 በላይ የትምህርትና ጤና ተቋማትን የፀሐይ ሃይል ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አዲስ አለም መብራቱ በበኩላቸው፥ ፕሮጀክቱ የስድስት ዓመታት ቆይታ ያለው መሆኑን ይገልጻሉ።
አምስት የተለያዩ ክፍሎች ያሉት ፕሮጀክቱ አዲስ አበባን ጨምሮ በ10 የሀገሪቱ ከተሞች የኤሌክተሪክ መስመር የማስፋፋት እና አቅም የማሳደግ ስራም በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ከ240 ሺህ በላይ የገጠሪቱን ህብረተሰብ ክፍል የታዳሽ ሃይል አማራጭ ተጠቃሚ የሚያደርግ አነስተኛ የሶላር ሃይል ማመንጫዎች ግንባታ መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ኢንጅነር ከበደ ጋኖሌ (ዶ/ር) እንዳሉት ፕሮጀክቱ በክልሉ ከዋናው ኤሌክትሪክ መስመር ርቀው የሚገኙ ሰባት ከተሞችን ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
በተቋማት በተገነቡ በጸሃይ ብርሃን የሚሰሩ ማቀዝቀዣዎች አማካይነትም አርሶ አደሩ ያመረተውን ፍራፍሬ በማቆየት ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በሚኒስቴሩ የተተከለውና 10 ኪሎ ዋት ኤልክትሪክ ሃይል በማመንጨት 150 ሄክታር መሬት እያለማ ያለው የሶላር ቴክኖሊጂም የአርሶአደሩን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡
በመድረኩ ከሲዳማ፣ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ደቡብ ኢትዮጵያና አሮሚያ ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን በፕሮጀክቱ አፈፃፀምና ቀጣይ አቅጣዎች ላይ ለሁለት ቀናት ይወያያሉ፡፡