ቀጥታ፡

አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው -ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 26/2017 (ኢዜአ)፡-አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገልጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሦስተኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በይፋ ከፍተዋል።

የኤክስፖው አካል የሆነ የፓናል ውይይት "የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዘመን እድሎችና ተግዳሮቶች" በሚል መሪ ሀሳብ ተካሒዷል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤መንግስት ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ውጤታማነት የፖሊሲ እና የአሰራር ማሻሻያዎች ሲያደርግ ቆይቷል።

በተለይም የግሉ ዘርፍ ምቹ የሆነ የብድር አቅርቦት እንዲያገኝ መደረጉን ጠቁመው፤በመጀመሪያ ምዕራፍ አገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች ውጤት ማምጣታቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪ እንደ አገር የኢኮኖሚውን ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ እንዲል ከማድረጉም በላይ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ እና ውጤታማ እንዲሆኑ አቅም መፍጠሩን ጠቁመዋል።

ለአብነትም የንግድ እና የኢንቨትመንት ህጎችን ለማሻሻል የተደረገውን ጠቅሰዋል።

ይህም አገሪቷ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንዲሁም የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በዘርፉ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማስቻሉን አንስተዋል።

ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) አያይዘውም፥ በኢኮኖሚው ዘርፍ በተለይም ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን ቀጣይነት ለማረጋገጥ በርካታ የሪፎርም ማሻሻያዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

ኢንዱስትሪው እኤኤ በ2030 የማምረት አቅም ወደ 85 በመቶ ለማሳደግ ግብ መቀመጡን ገልጸው፤ ለዚህም በመጀመሪያ ምዕራፍ የተደረገው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ዘመናዊ የኢኮኖሚ ስርዓት እንዲኖራት አቅም የፈጠረ እንደሆነ አንስተዋል።

ሪፎርሙም ኢንዱስትሪዎች ከውጭ ምንዛሬ ጋር በተያያዘ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም