የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ለውጥ እንዲያስመዘግብ አስችሏል- ሚኒስትር መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ለውጥ እንዲያስመዘግብ አስችሏል- ሚኒስትር መላኩ አለበል
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 26/2017 (ኢዜአ)፡-የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ለውጥ እንዲያስመዘግብ ማስቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሦስተኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ትናንት በይፋ ከፍተዋል።
የኤክስፖው አካል የሆነ የፓናል ውይይት "የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዘመን እድሎችና ተግዳሮቶች" በሚል ርዕስ ተካሒዷል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴሩ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም እንዲጨምር አድርጓል።
በተለይም የምርት ልማት እና ተወዳዳሪነትን በማሳደግ በኩል በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡
ወጪ ንግድን በማሳደግ እና ገቢ ምርትን በመተካት በግብዓት እና በምርት መካከል ያለውን ጥምረት ማሻሻል እንደተቻለ ጠቁመዋል።
ማሻሻያውን ተከትሎ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ሶስት ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶች በሀገር ውስጥ መመረታቸውንም ተናግረዋል።
ለስኬቱ መገኘት ቁልፉ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ መሆኑን ገልጸው፤ በተደረገው ማሻሻያ ምርትና ተወዳዳሪነትን መጨመር መቻሉንም አንስተዋል፡፡