የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ ስርዓትን በማስተካከል ኢንዱስትሪውን ውጤታማ አድርጓል-የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ ስርዓትን በማስተካከል ኢንዱስትሪውን ውጤታማ አድርጓል-የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 26/2017 (ኢዜአ)፡-የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ ስርዓትን በማስተካከል ኢንዱስትሪው በወጪ ንግድ አትራፊ እንዲሆን ማድረጉን የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሦስተኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ትናንት በይፋ ከፍተዋል።
የኤክስፖው አካል የሆነ የፓናል ውይይት "የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዘመን እድሎችና ተግዳሮቶች" በሚል ርዕስ ተካሒዷል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ በኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ላይ በተካሄደ ውይይት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢንዱስትሪውን በማነቃቃት ያስገኛቸውን ውጤቶች ዘርዝረዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለወጪ ምርት ትክክለኛውን ዋጋ በመስጠቱ ተወዳዳሪነትና ተጠቃሚነትን ማሳደግ ካስቻሉ ቁልፍ ተግባራት መካከል መሆኑን አስታውሰዋል።
ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን በማድረግ ለአምራች ኢንዱስትሪው የምንዛሬ አቅርቦት ዕድል ማስፋቱንም ገልጸዋል።
በዚህም የውጭ ምንዛሬ ስርዓትን በማስተካከል ኢንዱስትሪው በወጪ ንግድ አትራፊና ተወዳዳሪ መሆኑን የብሔራዊ ባንክ ገዢው ተናግረዋል።
ለወጪ ንግድ ትክክለኛው ዋጋ በመሰጠቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ የአገር ውስጥ አምራቾች መፈጠራቸውንም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው ዘርፍ እያስመዘገበች ያለውን ውጤት የበለጠ ለማጠናከር የሚያጋጥሙት ችግሮችን በቅንጅት መፍታት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የባንኩ ገዠ አረጋግጠዋል።
በኢንዱስትሪው የተፈጠረውን እድል በመጠቀም ከወጪ ንግድ የሚያገኘውን የውጭ ምንዛሬ የብሔራዊ ባንክን ህግ አክብሮ መስራት ተገቢ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የተዘረጋው የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ለምጣኔ ሃብት እድገት የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
የአገርን ምጣኔ ሃብት ለማሳደግና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ለሚደረገውን ጥረት የተፈጠረውን እድል በአግባቡ በመጠቀም ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።