የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር በመፍጠር ኢትዮጵያን ዋነኛ የአምራች ኢንዱስትሪ ማዕከል የሚያደርግ ነው - ሚኒስትር አህመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር በመፍጠር ኢትዮጵያን ዋነኛ የአምራች ኢንዱስትሪ ማዕከል የሚያደርግ ነው - ሚኒስትር አህመድ ሽዴ
አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 26/2017 (ኢዜአ)፡-የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጤናማ የፋይናንስ ስርዓትን በማጠናከር፣ ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር በመፍጠር እና መሠረተ ልማትን በማስፋፋት ኢትዮጵያን ዋነኛ የአምራች ኢንዱስትሪ ማዕከል እንደሚያደርግ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) 3ኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ትናንት በይፋ ከፍተዋል።
የኤክስፖው አካል የሆነ የፓናል ውይይት "የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዘመን እድሎችና ተግዳሮቶች" በሚል ርዕስ ተካሒዷል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በሰጡት ማብራሪያ፤ ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ ሆነው የቆዩ ዘርፎች በአገራዊ ለውጡ ዓመታት ክፍት መደረጋቸውን ገልጸዋል።
በአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ አምራች ኢንዲስትሪን ጨምሮ ሁሉንም የዕድገት ምንጮች በአግባቡ መጠቀምን መሠረት ያደረገ የፖሊሲ ዕይታ መተግበሩንም ጠቅሰዋል።
የግሉን ዘርፍ የኢኮኖሚው ዋና አንቀሳቃሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን በማንሳት፤የመንግሥት ሚና የግሉ ዘርፍ በዘላቂ ፋይናንስ እንዲመራና ቀጣይነት ያለው ውጤታማነትን ማረጋገጥ ላይ መሆኑን አብራርተዋል።
ከሰባት ዓመታት በፊት ለግሉ ዘርፍ አነስተኛ ፋይናንስ ይቀርብ እንደነበር በማውሳት፤አሁን ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ከሚያቀርበው ብድር ከ80 በመቶ በላይ ለግሉ ዘርፍ ሆኗል ብለዋል።
በዚህ የብድር አቅርቦት የአምራች ዘርፉ ተጠቃሚ መሆኑን በመጥቀስ፥ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉ የአምራች ኢንዱስትሪውን ከፍተኛ ተጠቃሚ አድርጓል ነው ያሉት።
የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ኢ- መደበኛ የንግድ ስርዓትን ወደ መስመር በማስገባት፣አምራቾችን በገበያው ውስጥ ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው፣የኢላማ ተኮር የኢንቨስትመንት ምቹ ምህዳር እና ቀጣናዊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ስራዎች ኢትዮጵያን ዋነኛ የአምራች ኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሎጂስቲክስና የትራንስፖርት መሰረተ ልማት፣ባቡር፣ አውሮፕላን ማረፊያዎች እና የየብስ መንገዶችን በከፍተኛ ሁኔታ ማስፋፋቱን ገልጸዋል።
የቴሌኮምና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን በከፍተኛ ሁኔታ ያሻሻሉ ሥራዎችን ማከናወኑንም ነው ያነሱት።
ሌላው መንግሥት ትኩረት የሰጠው ለተቋማት ግንባታ እንደሆነ በማንሳት፣ አገልግሎትን በዲጂታል ማዘመን ላይ የሰራው ስራ ለአምራች ኢንዱስትሪው መጠናከር ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።
የታክስ እፎይታን ጨምሮ የተለያዩ የማበረታቻ ሥርዓትን በመተግበር አምራች ኢንዱስትሪው ተጠቃሚ መሆኑንም አስረድተዋል።
አምራቾች የሀገር ውስጥ ገበያን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ከማድረግ ባሻገር፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያስተሳስሩ የትራንስፖርትና የኃይል መሰረተ ልማትን በመዘርጋት የኢትዮጵያ አምራቾች በቀጣናው ገበያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ፈሰስ የተደረገው ኢንቨስትመንትም ለአምራች ኢንዱስትሪው ዕድገት ወሳኝ አበርክቶ እንዳለው ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።